በክልሉ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ከ65 ሺህ በላይ የደረጃ “ሐ” ነጋዴዎች የንግድ ፈቃዳቸውን አድሰዋል---ቢሮው

አርባ ምንጭ ፤ ሐምሌ 30/2016 (ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ከ65 ሺህ በላይ የደረጃ “ሐ” ነጋዴዎች የንግድ ሥራ ፈቃድ ማደሳቸውን የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስታወቀ። 

ቁጥራቸው 20 ሺህ የሚጠጉ የደረጃ "ሐ" ነጋዴዎችም ፈቃዳቸውን በዲጂታል ሥርአት ማደሳቸው ተመላክቷል።

የቢሮው ሃላፊ አቶ ገሌቦ ጎልቶሞ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በክልሉ በደረጃ “ሀ” ”ለ” እና “ሐ” 139 ሺህ 120 ነጋዴዎች አሉ።

ከአጠቃላይ ነጋዴዎች ከ103 ሺህ በላይ የሚሆኑት የደረጃ “ሐ” ነጋዴዎች መሆናቸውን ገልጸው፣ ከእነዚህ ውስጥ 65 ሺህ 310 የሚሆኑት የንግድ ሥራ ፈቃዳቸውን በሐምሌ ወር አድሰዋል" ብለዋል።

የንግድ ሥራ ፈቃዳቸውን ካሳደሱት የደረጃ "ሐ" ነጋዴዎች መካከል 19ሺህ 986ቱ ዲጂታል ስርአቱን ተጠቅመው ፈቃዳቸውን ማሳደሳቸውንም አቶ ገሌቦ ገልጸዋል።

በክልሉ በሁሉም ዞኖች 112 የኦን ላይን ጣቢያዎች መቋቋማቸውን ጠቁመው፣ እስካሁን በ88ቱ ኦን ላይን የንግድ ፈቃድ እድሳት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አስታውቀዋል።

አቶ ገሌቦ እንዳሉት ፈቃዳቸውን ያላሳደሱ ቀሪ የደረጃ “ሐ” ነጋዴዎች በቀጣይ ቀናት ውስጥ ፈቃዳቸውን ሙሉ ለሙሉ እንዲያሳድሱ ለማድረግ ግብ ተይዞ እየተሠራ ነው።

በክልሉ ከሚገኙ 12 ዞኖች በንግድ ሥራ ፈቃድ እድሳት ቡርጂ፣ ኮንሶ እና ባስኬቶ ዞኖች የተሻለ አፈጻጸም ሲያስመዘግቡ፤ በኦን ላይን ስርአት ደግሞ አሪ፣ ጋሞ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ባስኬቶ እና ወላይታ ዞኖች ቀዳሚ መሆናቸውም ተገልጿል።

የባስኬቶ ዞን ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ደመወዝ ካንሶ በበኩላቸው የንግዱ ማህበረሰብ ፈቃዱን በጊዜ እንዲያድስ በየደረጃው የንቅናቄ ሥራ መሰራቱን አስታውሰው፣ እስካሁንም 82 በመቶ የሚሆነው ነጋዴ ፈቃዱን ማደሱን ጠቁመዋል።


 

በዞኑ በኦን ላይን ስርአት የፈቃድ እድሳት ሥራ ለመጀመሪያ ጊዜ መጀመሩን ጠቁመው፣ አስካሁንም 275 የደረጃ “ሐ” ነጋዴዎች ቴክኖሎጂን ተጠቅመው ፈቃድ ማደሳቸውን ገልጸዋል።

የደረጃ “ሐ” ነጋዴዎች የንግድ ፈቃድ እድሳት ሥራ በወረቀትና በዲጂታል ስርአት እየተከናወነ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የጋሞ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ሃላፊ ወይዘሮ ደሳለች ዳዊት ናቸው።


 

እንደእሳቸው ገለጻ የዲጂታል ሥርአቱ የነጋዴዎችን ጊዜና ወጪ ከመታደግ ባለፈ የንግድ ፈቃድ ዕድሳት ሥራውን የሚያቀላጥፍ ነው።

በዞኑ ሁሉንም ነጋዴዎች ወደ ዲጂታል ስርአት ለማስገባት በትኩረት እየተሠራ መሆኑንም ጠቅስዋል።

በአርባ ምንጭ ከተማ የባለ ሦስት እግር ባጃጅ ባለቤት ወጣት አብርሃም መስፍን ዲጂታል ስርአትን ተጠቅሞ የንግድ ሥራ ፈቃዱን ማደሱን ተናግሯል።


 

መንግስት ካለንበት ሆነን በዲጂታል ስርአት የንግድ ፈቃድ ለማደስ የሚያስችል አሰራር መፍጠሩ ሥራዬ እንዳይስተጓጎል በማድረጉ ደስተኛ ነኝ ብሏል።

ዲጂታል ስርአቱ በዘርፉ ይስተዋል የነበረን ያልተገባ የጥቅም ትስስር ያስቀረ በመሆኑ በቀጣይም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ወጣቱ ተናግሯል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም