በወንዶች የ3000 ሜትር መሰናክል ፍጻሜ ለሜቻ ግርማ፣ ጌትነት ዋለና ሳሙኤል ፍሬው ይወዳደራሉ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 1/2016(ኢዜአ)፦ በ33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በ3000 ሜትር መሰናክል ወንዶች ፍጻሜ አትሌት ለሜቻ ግርማ፣ አትሌት ጌትነት ዋለና አትሌት ሳሙኤል ፍሬው ውድድራቸውን ያደርጋሉ።

ለሜቻ በቶኪዮ በተካሄደው 32ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በርቀቱ ካሸነፈው ሞሮኳዊው አትሌት ሶፊያን ኤል ባካሊ ጋር የሚያደርጉት ፉክክር ይጠበቃል።

13ኛ ቀኑን በያዘው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ከምሽቱ 4 ሰዓት ከ43 ደቂቃ የ3000 ሜትር መሰናክል ወንዶች ፍጻሜ ውድድር ይካሄዳል።

አትሌት ለሜቻ ግርማ፣አትሌት ጌትነት ዋለና አትሌት ሳሙኤል ፍሬው ኢትዮጵያን ወክለው ይወዳደራሉ።

ውድድሩን የማሸነፍ የቅድሚያ ግምት ከተሰጣቸው አትሌቶች መካከል አንዱ የሆነው ለሜቻ ከአንድ ዓመት በፊት በፈረንሳይ ፓሪስ በተካሄደው ዳይመንድ ሊግ 7 ደቂቃ ከ52 ሴኮንድ ከ11 ማይክሮ ሴኮንድ የርቀቱን የዓለም ክብረ ወሰን አስመዝግቧል።

አትሌቱ ለ19 ዓመት በትውልድ ኬንያዊ በዜግነት ኳታራዊ በሆነው ሳኢፍ ሳኤድ ሻሄን (Saif Saaeed Shaheen) ተይዞ የነበረውን ክብረ ወሰን ነው በ1 ሴኮንድ ከ52 ማይክሮ ሴኮንድ ያሻሻለው።

በግንቦት ወር 2016 ዓ.ም በስዊድን ስቶክሆልም በተካሄደው የዳይመንድ ሊግ ውድድር 8 ደቂቃ ከ1 ሴኮንድ ከ63 ማይክሮ ሴኮንድ በርቀቱ የዓመቱን የዓለም ፈጣን ሰዓት አስመዝግቧል።

ለሜቻ በቶኪዮ በተካሄደው 32ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በርቀቱ የብር ሜዳሊያ ማግኘቱ የሚታወስ ነው።

ሌላኛው ተወዳዳሪ አትሌት ጌትነት ዋለ በግንቦት ወር 2016 ዓ.ም በሞሮኮ ራባት በተካሄደው ዳይመንድ ሊግ 8 ደቂቃ ከ5 ሴኮንድ ከ15 ማይክሮ ሴኮንድ ሁለተኛ በመውጣት የርቀቱን የግል ምርጥ ሰዓት አስመዝግቧል።

በኦሊምፒክ የመጀመሪያ ተሳትፎውን ያደረገው አትሌት ሳሙኤል ፍሬው በግንቦት ወር 2016 ዓ.ም በስዊድን ስቶክሆልም በተካሄደው የዳይመንድ ሊግ ውድድር 8 ደቂቃ ከ5 ሴኮንድ ከ78 ማይክሮ ሴኮንድ የርቀቱን የግል ምርጥ ሰዓት ማስመዝገብ ችሏል።

የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤት የሆነው አትሌት ለሜቻ ግርማ ከሞሮኳዊው አትሌት ሶፊያን ኤል ባካሊ ጋር በተደጋጋሚ የሚያደርጉት ፉክክር የተመልካቾችን ቀልብ የሚስብ ነው።

በቶኪዮ በተደረገው 32ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በ3000 ሜትር መሰናክል ወንዶች ፍጻሜ ኤል ባካሊ ለሜቻን በመቅደም የወርቅ ሜዳሊያ ማግኘቱ የሚታወስ ነው። ኢትዮጵያዊው አትሌት በወቅቱ የብር ሜዳሊያ ማግኘቱ አይዘነጋም።

ኤል ባካሊ በ18ኛው እና በ19ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች በርቀቱ የወርቅ ሜዳሊያዎችን አግኝቷል።

በተያያዘም ከቀኑ 6 ሰዓት ከ10 ደቂቃ ላይ የወንዶች 5000 ሜትር ማጣሪያ ይደረጋል። ሐጎስ ገብረሕይወት፣ ቢኒያም መሐሪና አዲሱ ይሁኔ በውድድሩ ላይ ይሳተፋሉ።

በምድብ 1 የሚወዳደረው አትሌት ሐጎስ በግንቦት ወር 2016 ዓ.ም በኖርዌይ ኦስሎ በተከናወነው ዳይመንድ ሊግ 12 ደቂቃ ከ36 ደቂቃ ከ73 ማይክሮ ሴኮንድ አንደኛ በመውጣት የርቀቱን የግል ምርጥ ሰዓት አስመዝግቧል። አትሌቱ የገባበት ጊዜ በርቀቱ የዓመቱ የዓለም ፈጣን ሰዓት ነው።

ሐጎስ በኦሊምፒክ የተሳተፈው እ.አ.አ በ2012 በለንደን በተካሄደው 30ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ነበር። እ.አ.አ በ2016 በሪዮ ዴጄኔሮ በተደረገው 31ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በ5000 ሜትር የነሐስ ሜዳሊያ አግኝቷል።

በኦሊምፒክ የመጀመሪያ ተሳትፎውን የሚያደርገው አትሌት ቢኒያም መሐሪ በግንቦት ወር 2016 ዓ.ም በአሜሪካ ሎስ አንጀለስ በተካሄደ ውድድር 12 ደቂቃ ከ54 ሴኮንድ ከ10 ማይክሮ ሴኮንድ የርቀቱን የግል ምርጥ ሰዓት አስመዝግቧል።

ሌላኛው ተወዳዳሪ አዲሱ ይሁኔ በግንቦት ወር 2016 ዓ.ም በኖርዌይ በተካሄደው የዳይመንድ ሊግ ውድድር 12 ደቂቃ ከ49 ሴኮንድ ከ65 ማይክሮ ሴኮንድ የርቀቱን የግል ምርጥ ሰዓት ማስመዝገቡ የሚታወስ ነው።

አትሌት ቢኒያምና አትሌት አዲሱ በማጣሪያው በምድብ 2 ይወዳደራሉ። 

በሁለት ምድብ በሚካሄደው ማጣሪያ ከየምድቡ ከአንድ እስከ ስምንት የሚወጡ አትሌቶች ለፍጻሜ ያልፋሉ። የፍጻሜው ውድድር ነሐሴ 4 ቀን 2016 ዓ.ም ከምሽቱ 2 ሰዓት ከ50 ደቂቃ ላይ ይደረጋል።

የ5000 ሜትር የዓለም ክብረወሰን ባለቤት ዩጋንዳዊው ጆሹዋ ቼፕቴጋይና ሌላኛው ዩጋንዳዊ አትሌት ጃኮብ ኪፕሊሞ በ10000 ሜትር ወንዶች የፍጻሜ ውድድር በመድከማቸው ምክንያት ከማጣሪያው ውድድር ውጪ መሆናቸውን የዩጋንዳ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።  

በተጨማሪም አትሌት ብርቄ ኃየሎም ከቀኑ 7 ሰዓት ከ45 ደቂቃ ላይ በ1500 ሜትር ሴቶች የሁለተኛ ዙር ማጣሪያ (Repechage Round) በድጋሚ ለግማሽ ፍጻሜ ለማለፍ ትወዳደራለች።

ብርቄ በማጣሪያው በምድብ 1 ትገኛለች። አትሌቷ ትናንት በተካሄደው የ1500 ሜትር የመጀመሪያ ዙር ማጣሪያ 4 ደቂቃ ከ7 ሴኮንድ ከ15 ማይክሮ ሴኮንድ 11ኛ መውጣቷ ይታወቃል።

በሁለት ምድብ ተከፍሎ በሚካሄደው የማጣሪያ ውድድር ከየምድቡ ከአንድ እስከ ሶስት የሚወጡ አትሌቶች ግማሽ ፍጻሜውን ይቀላቀላሉ።

አትሌት ጉዳፍ ፀጋይና አትሌት ድርቤ ወልተጂ በመጀመሪያው ዙር ማጣሪያ ከየምድባቸው አንደኛ በመውጣት በቀጥታ ለግማሽ ፍጻሜ ማለፋቸው ይታወቃል።

የግማሽ ፍጻሜ ውድድሩ ሐሙስ ነሐሴ 2 ቀን 2016 ዓ.ም ከምሽቱ 2 ሰዓት ከ35 ደቂቃ ላይ ይደረጋል።

በተያያዘም ትናንት በተደረገ የሴቶች የ3000 ሜትር መሰናክል የፍጻሜ ውድድር አትሌት ሲምቦ አለማየሁ አምስተኛና ሎሚ ሙለታ ስምንተኛ ደረጃን በመያዝ ውድድራቸውን አጠናቀዋል።

ኢትዮጵያዊ በ33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች እስካሁን ሁለት የብር ሜዳሊያዎችን በማግኘት በሜዳሊያ ሰንጠረዡ 52ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም