ቀጥታ፡

በ3000 ሜትር መሰናክል የኢትዮጵያ አትሌቶች ሜዳሊያ ውስጥ አልገቡም

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 30/2016(ኢዜአ)፦ በ33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በ3000 ሜትር የሴቶች መሰናክል ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድል አልቀናቸውም፡፡

አትሌት ሲምቦ 9 ደቂቃ ከ00 ሴኮንድ ከ83 ማይክሮ ሴኮንድ አምስተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች። በርቀቱ የራሷን የዓመቱን ፈጣን ሰዓት አስመዝግባለች።

አትሌት ሎሚ 9 ደቂቃ ከ06 ሴኮንድ ከ07 ማይክሮ ሴኮንድ ስምንተኛ ደረጃን ይዛለች። ሎሚ የርቀቱን የግል ምርጥ ሰዓቷን ማሻሻል ችላለች።

በትውልድ ኬንያዊ በዜግነት ባህሬናዊ የሆነችው ዊንፍሬድ ሙቲል ያቪ 8 ደቂቃ ከ52 ሴኮንድ ከ76 ማይክሮ ሴኮንድ አንደኛ በመውጣት የወርቅ ሜዳሊያ አግኝታለች። ከድሉ በተጨማሪ አትሌቷ የርቀቱን የኦሊምፒክ ክብረ ወሰን ሰብራለች።

ዩጋንዳዊቷ አትሌት ፔሩዝ ቼሙታይ 8 ደቂቃ ከ53 ሴኮንድ ከ34 ማይክሮ ሴኮንድ ሁለተኛ ደረጃን ይዛለች። ቼሙታይ በርቀቱ የአገሯን ብሔራዊ ክብረ ወሰን መስበር ችላለች።

ኬንያዊቷ አትሌት ፌዝ ቼሮቲች 8 ደቂቃ ከ55 ሴኮንድ ከ15 ማይክሮ ሴኮንድ ሶስተኛ በመውጣት የነሐስ ሜዳሊያ ባለቤት ሆናለች። የርቀቱን የግል ምርጥ ሰዓቷንም አሻሽላለች።

በውድድሩ ላይ 15 አትሌቶች ተሳትፈዋል።

ኢትዮጵያ በ33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች እስካሁን ሁለት የብር ሜዳሊያዎችን አግኝታለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም