ቀጥታ፡

የኢትዮጵያና የኮሪያ ሪፐብሊክ ዘመናትን ያስቆጠረ ታሪካዊ ግንኙነት ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኢንጂነር አይሻ መሀመድ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 30/2016(ኢዜአ)፦ለረጅም ዘመን የዘለቀው የኢትዮጵያና የኮሪያ ሪፐብሊክ ግንኙነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ ገለጹ።

ሚኒስትሯ በኮሪያ ሪፐብሊክ የአርበኞች እና የቀድሞ ወታደሮች ጉዳይ ሚኒስትር ካንግ ጁንግ የተመራውን የልዑካን ቡድን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

በውይይታቸውም የሁለቱ ሀገራት ታሪካዊ ግንኙነት ዘመናትን ያስቆጠረ መሆኑንና ይህንን ታሪካዊ ግንኙነት ይበልጥ ሊያጠናክሩ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይም በቀጣይ አብሮ ለመስራት ፅኑ ፍላጎት መኖሩ ተመላክቷል።


 

ኢንጂነር አይሻ በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ ወታደር በኮሪያ ሪፐብሊክ የሰላም ማስከበር ግዳጅ በተሰማራበት ጊዜ የፈፀመው ወታደራዊ ጀብዱና የሰንደቅ-ዓላማ ፍቅር እስከ አሁን ድረስ ሁለቱም ሀገራት የሚኮሩበት ድንቅ ተግባር መሆኑንም አስታውሰዋል።

ይህንን ታሪክ በሚያከብር መልኩም ለረጅም ጊዜ የዘለቀውን የሁለቱን ሀገራት ወታደራዊ ግንኙነት የበለጠ አጠናክሮ ማስቀጠል ተገቢ መሆኑንም ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የኮሪያ ሪፐብሊክ ወታደራዊ አታሼ ቢሮ የዓርበኞችና የቀድሞ ወታደሮች ጉዳይ ሚኒስትር ካንግ ጁንግ በበኩላቸው ወደ ኢትዮጵያ በመምጣታቸውና የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት የበለጠ የሚያጠናክር ውይይት በማድረጋቸው ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል።

የሁለቱ አገራት ወዳጅነትና ታሪካዊ ትስስር አሁን ላለው ትውልድ ብቻ ሳይሆን ለቀጣይ ትውልድም መሻገር ያለበት በመሆኑ የጋራ ታሪካችን ተሰንዶ ሊቀመጥ ይገባል ብለዋል፡፡

በሚኒስቴሩ ለተደረገላቸው አቀባበልም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በዚሁ ውይይት ላይ የመከላከያ ፋይናንስ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ማርታ ሉዊጂን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንንኖች መገኘታቸውን ከመከላከያ ሰራዊት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም