ቀጥታ፡

የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት አሰጣጥን በሰው ሰራሽ አስተውሎት ለማገዝ የሚያስችል ውይይት ተደረገ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 30/2016(ኢዜአ)፦ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት አሰጣጥን በሰው ሰራሽ አስተውሎት የታገዘ ለማድረግ የሚያስችል ውይይት ከኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በውይይቱ ላይ እንደገለጹት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ዘርፉን አዎቶሜት በማድረግ ላይ መሆኑንና የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን እና የኤልክትሮኒክስ ንግድ(E-commerce) የሚዳብርበት ስርዓት እየተዘጋጀ ነው።


 

ይህንንም በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ በመታገዝ ይበልጥ ቀላልና ምቹ ማድረግ ቅንጦት ሳይሆን ወቅቱ የሚጠይቀው አሰራር ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ኢ/ር ዶ/ር) በበኩላቸው ሚኒስቴሩ እየተጠቀመባቸው ባሉ ቴክኖሎጂዎች ላይ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማከል የሀገሪቱን የንግድ ስርዓት ለማዘመን ኢኒስቲትዩቱ የበኩሉን አስተዋፅዎ ያደርጋል ነው ያሉት።

አክለውም በመረጃ ላይ የተደገፈ ትክክለኛ ውሳኔ ለመስጠት አርቲፊሻል ኢንተለጀንስን መጠቀም እንደሚያስፈልግ መግለጻቸውን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም