ቀጥታ፡

የአድዋ ድል መታሰቢያ ለጥቁር ህዝቦች ነፃነት የተከፈለውን ዋጋ በቋሚ ቅርስነት የሚዘክር ነው- ተመራማሪዎች

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 30/2016(ኢዜአ)፦የአድዋ ድል መታሰቢያ ለጥቁር ህዝቦች ነፃነት የተከፈለውን ዋጋ በቋሚ ቅርስነት የሚዘክር መሆኑን የተለያዩ አገራት ተመራማሪዎች ገለጹ።

የሉሲ ወይም ድንቅነሽ ቅሪተ አካል የተገኘችበትን 50ኛ ዓመት ለመዘከር በተዘጋጀው መርሐ ግብር የታደሙ ዓለም አቀፍ ተመራማሪዎች የአድዋ መታሰቢያን ጨምሮ የተለያዩ ታሪካዊ ስፍራዎችን ጎብኝተዋል።


 

በጉብኝቱ ላይ ከተገኙት መካከል ኢዜአ ያነጋገራችው ተመራማሪዎች፤ የአድዋ ድል መታሰቢያ ታሪክን ከመዘከር ያለፈ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያለው መሆኑን ገልጸዋል።  

በአሜሪካ ዱክ ዩኒቨርሲቲ የሰው ዘር አመጣጥ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ቻርልስ ሙሲባ፤ አድዋ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የመላ አፍሪካ የጋራ ታሪክና የኩራት መገለጫ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የአድዋ ድል ከኢትዮጵያዊያን ክብርና ነጻነት ዓርማነቱ ባሻገር አፍሪካውያን በ1960ዎቹ ከነበሩበት የቅኝ ግዛት ቀንበር ነጻ እንዲወጡ መንገድ የጠረገ ድል መሆኑንም አንስተዋል።

በመሆኑም ይህንን የገዘፈ ታሪክ የሚዘክር መታሰቢያ መገንባቱ ቋሚ ቅርስና ትልቅ የቱሪዝም ሃብት ነው ብለዋል።


 

የሉሲ (ድንቅነሽን) ቅሪተ አካል ያገኙት አሜሪካዊው ፕሮፌሰር ዶናልድ ጆንሰን፤ አድዋ ኢትዮጵያውያን ለሕልውናቸው ያደረጉትን አኩሪ ተጋድሎ ለመዘከር የተገነባ ቋሚ ቅርስ መሆኑን ገልጸዋል።

መላ አፍሪካውያን ይህን መታሰቢያ በመጎብኘት የታሪኩን ትልቅነትና የጋራ ሃብትነት በቅጡ ሊገነዘቡት ይገባል ብለዋል።

'ታሪክ በባለታሪኩ መጻፍ ይገባዋል' ያሉት ፕሮፌሰሩ፤  አድዋ መታሰቢያ ደግሞ ያልተነገሩ የደቡብ ክፍለ ዓለም ታሪኮችን ለመተረክ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ጠቁመዋል።

የአድዋ ድል መታሰቢያ ከቤተ-መዘከርነት ባሻገር ዘርፈ ብዙ አገልግሎት የሚሰጡ ክፍሎችን መያዙም ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።


 

የዩጋንዳ ብሔራዊ ሙዚዬም ባልደረባ ሰቪኖ ክርስቶፎር፤ ኢትዮጵያንና መሰል ጥንታዊ ታሪክ ያላችውን አገሮች የመጎብኘት ህልሜ በመሳካቱ ተደስቻለሁ ብለዋል።

የአድዋ ድል መታሰቢያ ኢትዮጵያዊያን ለመላ ጥቁር ህዝቦች ነፃነት የፈፀሙትን ጀግንነትና የከፈሉትን ዋጋ የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በእንግሊዝ የሊቨርፑል ዩኒቨርሲቲ የሰው ዘር አመጣጥ ከፍተኛ ተመራማሪ ኢግናሲዮ ላሳጋባስተር (ዶ/ር)፤ መታሰቢያው የአድዋን ታሪክ ዘመኑን በዋጀ ቴክኖሎጂ በቅጡ የተደራጀበት እንደሆነ ገልጸዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም