ቀጥታ፡

የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት የ ISO 9001 የብቃት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ተሸላሚ ሆነ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 30/2016 (ኢዜአ)፦ የኢፌዴሪ ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት የ ISO 9001: 2015 የብቃት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ተሸላሚ ሆነ፡፡

የብቃት ማረጋገጫ ሽልማቱን የሰጠው የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት ነው፡፡

የኢፌዴሪ ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት  ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ከድር(ዶ/ር) በሽልማት ሥነ-ሥርዓቱ ወቅት እንዳሉት፤ ኢንስቲትዩቱ የተሸለመው የ ISO 9001: 2015 የብቃት ማረጋገጫ መስፈርትን አሟልቶ በመገኘቱ ነው፡፡


 

በ2016 በጀት ዓመት ዓለም አቀፍ የጥራት ሥራ አመራር ፍልስፍናን ለመተግበር አቅዶ ሲሰራ መቆየቱን አውስተዋል፡፡

ለተፈጻሚነቱም አጠቃላይ ለኢንስቲትዩቱ ማኅበረሰብ በሙሉ የተቋሙን ራዕይ በግልጽ በማሳወቅ እና ሥልጠናዎችን በመስጠት ወደ ሥራ መገባቱን አመላክተዋል፡፡

በዚህም ኢንስቲትዩቱ ለትምህርት አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን የማሟላት፣ ብቃት ያላቸው መምህራንን የማፍራትና ተደራሽነቱን የማስፋት ሥራ  መሥራቱን ገልፀዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ጥራት ያላቸው ሥልጠናዎችን የመስጠት፣ ጥናትና ምርምሮችን የማካሄድ ተግባራትን ማከናወኑንና የማኅበረሰብ አገልግሎት መስጠቱን ጠቁመዋል፡፡

እነዚህ ተግባራት ተደማምረው ለሽልማት እንዳበቁት የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ፤ የብቃት ማረጋገጫ ሽልማቱ በቀጣይ ከዚህም በላይ ለመሥራት መነሳሳትን እንደሚፈጥርላቸው ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት የሰርቲፊኬሽን ዳይሬክተር አምሳሉ እንየው በበኩላቸው፤ ISO 9001: 2015 ተቋማት የተሰጣቸውን ኃላፊነት በጥራት መፈጸማቸውን ማረጋገጫ መስፈርት ነው ብለዋል፡፡


 

ለኢፌዴሪ ቴክኒክና ሙያ ኢንስቲትዩት የብቃት ማረጋገጫ ሰርቲፊኬት የተሰጠው ይህን ተግባር አከናውኖ በመገኘቱ መሆኑን ገልፀዋል።

ድርጅቱ ከሽልማቱ በፊት ኦዲተሮችን መድቦ ሥራው በትክክል መሠራቱን የማረጋገጥ ሥራ ማከናወኑን አመላክተው፤ የኦዲት ግኝቱ የተሟላ ሆኖ በመገኘቱ ሽልማት መሰጠቱን ጠቁመዋል፡፡

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተሻለ በሬቻ (ዶ/ር) መንግሥት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሆኑ ሰልጣኞችን ለማፍራት በርካታ የሪፎርም ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡


 

የኢፌዴሪ ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩት ዛሬ ያገኘው የብቃት ማረጋገጫ ሰርቲፊኬትም የዚሁ ሪፎርም አንድ አካል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሽልማቱ የኢንስቲትዩቱን ዓለም አቀፋዊነት የሚያረጋግጥ እና ከኢንስቲትዩቱ ተመርቀው የሚወጡ ሰልጣኞች በየትኛውም ዓለም ተቀጥረው እንዲሰሩ ዕድል የሚከፍት ነው ብለዋል፡፡

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም