የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሀገር ምልክትነቱም ባለፈ በአየር ትራንስፖርት ኢንዱስትሪ የስኬት መንገዱን አጠናክሮ ቀጥሏል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሀገር ምልክትነቱም ባለፈ በአየር ትራንስፖርት ኢንዱስትሪ የስኬት መንገዱን አጠናክሮ ቀጥሏል
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 30/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሀገር ምልክትነቱም ባለፈ በዓለም የአየር ትራንስፖርት ኢንዱስትሪ ዘርፍ የስኬት መንገዱን አጠናክሮ መቀጠሉን በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ ገለጹ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ አሁን ላይ በ136 ዓለም አቀፍና 22 የአገር ውስጥ የበረራ መዳረሻዎች አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል።
በስካይ ትራክስ ዓለም አቀፍ የንግድ ድርጅት የ2024 ምርጡ የአፍሪካ አየር መንገድ ሽልማት አሸናፊ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለ7 ተከታታይ አመታትም የአፍሪካ ምርጡ አየር መንገድ መሆን ችሏል።
በ2016 በጀት ዓመትም አጠቃላይ 577 ሺህ 746 የበረራ ሰዓት በማስመዝገብ 7 ነጥብ 02 ቢሊየን ዶላር ገቢ በማግኘት በስኬት መንገድ ቀጥሏል።
የአየር መንገዱን አጠቃላይ እንቅስቃሴና ፋይዳውን በተመለከተ ኢዜአ በመንግስታቱ ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ ጋር ቆይታ አድርጓል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሀገርም አልፎ የአፍሪካ ኩራት ሆኖ መቀጠሉን የገለጹት አምባሳደሩ፤ በዓለም የአየር ትራንስፖርት ኢንዱስትሪ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ግዙፍ ተቋም መሆኑን ገልጸዋል።
አየር መንገዱ በአገልግሎቱ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ትስስር ከመፍጠር ባሻገር የሀገር ምልክት ሆኖ ኢትዮጵያን በማስተዋወቅ የላቀ ሚና እያበረከተ ይገኛል ብለዋል።
በዓለም ግዙፉ የአውሮፕላን አምራች ኩባንያ ቦይንግ የአፍሪካ አህጉር ዋና ጽህፈት ቤቱን በአዲስ አበባ ለመክፈት መዘጋጀቱም ሌላ ተጨማሪ ስኬት መሆኑን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ እኤአ በ2035 ዓመታዊ ገቢውን 25 ቢሊየን ዶላር በማድረስ በዓመት 67 ሚሊየን መንገደኞችን ለማጓጓዝ ራዕይ ሰንቆ እየሰራ ይገኛል።