ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ጋር በጋራ ለመሥራት ተፈራረመ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 30/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን በጋራ ለመሥራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ሥምምነት ተፈራረመ። 

ሥምምነቱን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ቤተልሔም አበባው እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀማል ረዲ ፈርመውታል።

ሥምምነቱ ሁለቱ ተቋማት ሙስናን ለመከላከል መረጃን ለኅብረተሰቡ ተደራሽ በማድረግ፣ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ለመሥራት እንዲሁም በትውልድ ሥነ-ምግባር ግንባታ በጋራ ለመሥራት የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል። 

የኢዜአ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ቤተልሔም አበባው በዚሁ ጊዜ፤ ኢዜአ መልካም ሥነ-ምግባር ያለው ትውልድ ለመገንባትና ሙስናን ለመከላከል መረጃዎችን ተደራሽ በማድረግ የጀመረውን ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል። 


 

ጎን ለጎንም ሕብረተሰቡ በፀረ-ሙስና ትግሉ ላይ ያለውን ግንዛቤ በማሳደግ የፀረ-ሙስና ትግሉ ውጤታማ እንዲሆን ኢዜአ ለኅብረተሰቡ መረጃ ተደራሽ በማድረግ የሚያበረክተውን አስተዋጽዖም ይበልጥ እንደሚያጠናክር አረጋግጠዋል።  

ከዚህ አንጻር ዛሬ በሁለቱ ተቋማት የተደረሰው ሥምምነት ከዚህ በፊት በጋራ ሲሰሩ የነበሩትን ሥራዎች የበለጠ ለማጠናከርና በፀረ-ሙስና ትግሉ የሕዝቡን ተሳትፎ በማረጋገጥ ሙስናን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል።   

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀማል ረዲ በበኩላቸው፤ የመግባቢያ ሥምምነቱ ሙስናን በመከላከል ረገድ ከኢዜአ ጋር የተጀመሩትን ሥራዎች የበለጠ ለማጠናከር ያለመ ነው ብለዋል።


 

በተለይም በፀረ-ሙስና ትግሉ መረጃን ተደራሽ በማድረግና ሕዝቡን በማሳተፍ የሚሰሩ ቅንጅታዊ ሥራዎችን ውጤታማ ለማድረግ ሥምምነቱ ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ነው ኮሚሽነሩ ያብራሩት።  

 

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም