በሰው መነገድና ሰውን በህገ ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀሎችን ለመከላከል በጋራ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሰው መነገድና ሰውን በህገ ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀሎችን ለመከላከል በጋራ እየተሰራ ነው

አዳማ፤ ሐምሌ 30/2016 (ኢዜአ)፦ በሰው መነገድና ሰውን በህገ ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀሎችን ለመከላከል በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የፍትህ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ብሔራዊና ክልላዊ የፍልሰት ትብብር ጥምረት የ2016 በጀት ዓመት የዕቅድ ክንውንና ቀጣይ ትኩረት ላይ የባለድርሻ አካላት የውይይት መድረክ በአዳማ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
የፍትህ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ በላይሁን ይርጋ በመድረኩ ላይ እንደገለፁት መደበኛ ባልሆነ መንገድ ከሀገር የሚወጡ ዜጎች ለተለያየ ሰብዓዊ መብት ጥሰትና ብዝበዛ ይዳረጋሉ።
በዚህም ለተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ህገወጥ የሰው አዘዋዋሪዎች በመጋለጥ ለችግር እየተዳረጉ መሆኑን ገልጸዋል።
ለዚህም ሲባል በሰው መነገድና ሰውን በህገ ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀሎችን በተቀናጀ መልኩ ለመከላከል እየተሰራ ነው ብለዋል።
የተለያዩ የህግ ማዕቀፎችና ስትራቴጂዎችን በማዘጋጀት ወደ ትግበራ ከመግባት ባለፈ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ተፈፃሚ እየተደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ህገ ወጥ ፍልሰትን ለመከላከል በተደረጉ ጥረቶች አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን አውስተው በሰው መነገድና ሰውን በህገ ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀልን በተመለከተ የተከፈቱ 361 የክስ መዝገቦች ላይ በፌዴራልና በክልሎች ውሳኔ መሰጠቱን ገልጸዋል።
በፍትህ ሚኒስቴር ከፍተኛ አቃቤ ህግና የጥምረቱ አስተባባሪ አቶ አቤል ገብረእግዚአብሔር በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከፍትህ አካላትና በየደረጃው ከሚገኙ ባለድርሻዎች ጋር አበረታች ስራዎች ተሰርተዋል ብለዋል።
በተለይ የአቅም ግንባታና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎች ለፖሊሶች፣ ለኃይማኖት አባቶች፣ ለወጣቶችና ለሴቶች መሰጠቱን ገልጸዋል።
እንዲሁም የኢሚግሬሽን ባለሙያዎች በህገ ወጥ ፍልስት ምክንያት እየደረሰ ያለውን ጉዳት እንዲገነዘቡና ችግሩን ለመቅረፍ በሚሰሩ ስራዎች ውስጥ ግንባር ቀደም ተዋናይ እንዲሆኑ የግንዛቤ ማጎልበቻ ስልጠና ተሰጠቷል ብለዋል።
በክልሎችና በፌዴራል በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ረገድ ከቀረቡት 802 የክስ መዝገቦች ውስጥ 361 በሚሆኑት ላይ ውሳኔ መሰጠቱን ጠቅሰው በዚህም እንደየጥፋታቸው እስከ 20 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲሁም እስከ 410 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት ውሳኔ ተላልፎባቸዋል ብለዋል።
በተመሳሳይም ሳኡዲ አረቢያን ጨምሮ 22 ሀገራት 116 ሺህ 996 ዜጎች ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውን ጠቅሰዋል።
ለዚህም መንግስት ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ከማድረጉም ባለፈ ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር የጤና፣ የትራንስፖርትና ሌሎች አገልግሎቶችን በመስጠት ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲቀላቀሉ ማድረጉን አመልክተዋል።
28 ሺህ 380 ከስደት ተመላሾች የስራ ዕድል ማግኘታቸውን ጠቅሰው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 320 ሺህ ዜጎች በህጋዊ መንገድ ወደ ውጭ ሀገር ለስራ ስምሪት መሄዳቸውን አስታውሰዋል።
የውጭ ሀገር የስራ ስምሪት መዳረሻን ለማስፋት ከ12 ሀገራት ጋር የመግባቢያ ስምምነት ለመፈፀም እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
በመድረኩ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖን ጨምሮ ከፌዴራልና ከክልል የተውጣጡ የትብብር ጥምረቱ አባል ሴክተር መስሪያ ቤቶች፣ አመራሮችና የስራ ኃላፊዎች ተሳታፊ ሆነዋል።