የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ትግበራው የገንዘብና የፊሲካል ፖሊሲ አቅምን የሚገነባና የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ሥርዓትን የሚያዘምን ነው - ኢዜአ አማርኛ
የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ትግበራው የገንዘብና የፊሲካል ፖሊሲ አቅምን የሚገነባና የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ሥርዓትን የሚያዘምን ነው
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 30/2016 (ኢዜአ)፦ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ትግበራው የገንዘብና የፊሲካል ፖሊሲ አቅምን የሚገነባና የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ሥርዓትን የሚያዘምን መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር እና የፕላንና ልማት ሚኒስቴር የተለያዩ የሥራ ኃላፊዎች ገለጹ።
መንግሥት ቀጣይነት ያለው ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማስመዝገብና የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ትግበራን በተሟላ መልኩ በይፋ ማስጀመሩ ይታወቃል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ትግበራውን በተመለከተም ኢዜአ ከገንዘብ ሚኒስቴር እና ፕላንና ልማት ሚኒስቴር የሚመከለታቸው የሥራ ኃላፊዎች ጋር ቆይታ አድርጓል።
በገንዘብ ሚኒስቴር የፊሲካል ፖሊሲ አማካሪ መዝገቡ አምሃ፤ የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ያመጣውን ስኬት አንስተዋል።
በመጀመሪያው ምዕራፍ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የተመዘገቡ ስኬቶችን ለማስቀጠል ሁለተኛው ምዕራፍ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ተግባር ላይ እንዲውል ተደርጓል ብለዋል።
የኢትዮጵያን የምጣኔ ኃብት እድገት በተሟላ መልኩ ለማስቀጠልም አሁን ላይ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ሙሉ ትግበራ ይፋ መደረጉን ገልፀዋል።
የፖሊሲው ሙሉ ትግበራም የኃብት ብክነትን በማስቀረት ምርታማነትን በማሳደግና ኢንቨስትመንትን በማሳደግ ረገድ አስተዋጽዖ የላቀ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የውጭ ምንዛሬና የክፍያ ሚዛንን እንዲሁም የፊሲካል ደኅንነትን በማስጠበቅ የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል።
በፕላንና ልማት ሚኒስቴር የልማት ዕቅድና የመንግሥት ኢንቨስትመንት አስተዳደር ሥራ አስፈጻሚ በረከት ፍስሃፅዮን፤ የአሥር ዓመት የልማት ዕቅድ በመንደፍ የመጀመሪያው ምዕራፍ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ተግባራዊ መደረጉን አስታውሰዋል።
በመጀመሪያ ምዕራፍ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ በታክስ አሰባሰብ፣ በመንግሠት ወጪ አስተዳደርና ተያያዥ የኢኮኖሚ መስኮች ውጤት ተመዝግቦበታል ብለዋል።
በመሆኑም የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ሙሉ ትግበራ በጠንካራ ሲቪል ሰርቪስ የገንዘብና የፊሲካል ፖሊሲ አቅምን በመገንባት የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ሥርዓትን ለማዘመን የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል።
በማክሮ ኢኮኖሚክ ፖሊሲ ትግበራው መንግሥት የነዳጅ፣ ማዳበሪያ፣ ዘይት፣ መድኃኒትና ሌሎችም ላይ ድጎማ ማድረጉ ጉልህ ፋይዳ ያለው መሆኑን አማካሪው አንስተዋል።
የግሉን ዘርፍ የውጭ ምንዛሬ ፍላጎት ምላሽ በመስጠት የተሻለ የምርታማነትና የግብዓት አቅርቦት እንዲኖር የሚያስችል መሆኑንም ይሆናል ሲሉ አቶ በረከት ብለዋል።
በፖሊሲ ትግበራው መነሻነት ከልማት አጋር አገራትና ተቋማት የሚገኝ የገንዘብ ድጋፍ በተሟላ መልኩ ለታለመለት ልማት ለማዋል ዝግጅት መደረጉን አንስተዋል።
ለተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ትግበራው ስኬታማነትም በተለይም ምሁራን፣ የፍትሕ ተቋማት፣ የንግዱ ማኅበረሰብ አጠቃላይ ዜጎች የሚጠበቅባቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።