የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ትግበራው የተረጋጋ፣ የተሟላና ቀጣይነት ያለው ሀገራዊ እድገት የሚያመጣ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ትግበራው የተረጋጋ፣ የተሟላና ቀጣይነት ያለው ሀገራዊ እድገት የሚያመጣ ነው
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 30/2016(ኢዜአ)፦ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ትግበራው የተረጋጋ፣ የተሟላና ቀጣይነት ያለው ሀገራዊ እድገት የሚያመጣ መሆኑን ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ገለጹ።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ፤ በመጀመሪያና በ2ኛው ምዕራፍ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሂደት ወደ ተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ትግበራ ለመግባት ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን ገልጸዋል።
የማሻሻያ ሂደቱም ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ)ና ዓለም ባንክን ጨምሮ በዓለም አቀፍ አጋሮች ድጋፍ የሚተገበር መሆኑን ተናግረዋል።
የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፉ በገበያው እንዲመራ፣ ዕዳን በማቃለል፣ የገንዘብና ፋይናንስ ፖሊሲ፣ የመንግስት ገቢና ወጪ ፊስካል ፖሊሲን በማሻሻልና ዕዳን በማቃለል የላቀ ጠቀሜታ አንዳለው አንስተዋል።
የፖሊሲ ትግበራው የዋጋ ንረትና የምንዛሬ ገበያ መዋዠቅን እንዲሁም የአጭር ጊዜ ጫናን በመቋቋም የተረጋጋ ኢኮኖሚ መፍጠር ዋነኛ ዓላማው መሆኑንም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የፐብሊክ ፋይናንስ ስርአቷ የተሻለ ግልጽና ውጤታማ መሆኑን ገልጸው በዚህ ሪፎርም ጫና የሚደርስባቸውን ወገኖች የደሞዝ ጭማሪን ጨምሮ ድጎማ የሚደረግ መሆኑን ገልጸዋል።
የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)፤ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርም ሀሳቦች ተቀርጸው ባለፉት ስድስት ዓመታት በተለያየ ደረጃ ሲተገበር መቆየቱን ገልጸዋል።
በዚህም መዋቅራዊ በሆኑ የአሰራር ግድፈቶች ታንቆ የነበረውን የግሉን ዘርፍ በማነቃቃት የኢኮኖሚው መሪ የሚሆንበት ሁኔታ መፈጠሩን ጠቁመዋል።
የፕሮጀክቶች ግንባታ በታለመላቸው ጊዜ ጥራትና በተመደበላቸው ሀብት ማጠናቀቅ መቻሉን አንስተው የነበሩ ልምምዶች ለተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ትግበራ ጥሩ መነሻ እና አስቻይ ሁኔታ ይሆናሉ ብለዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ፤ ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ የተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚ እንዲኖር በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን አንስተዋል።
በዚህም የእዳ ጫናን ለመቀነስ መሰረታዊ ስራዎች መከናወናቸውንና ትልቅ ለውጥ የተገኘበት መሆኑን አስታውሰው ለግሉም ዘርፍ ተገቢውን ብድር መስጠት ተችሏል ብለዋል።
በመሆኑም የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ትግበራው የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ የተረጋጋ፣ የተሟላና ቀጣይነት ያለው እድገት እንዲመዘገብ የሚያደረግ መሆኑን አስረድተዋል።