ቀጥታ፡

በሴቶች የ3000 ሜትር መሰናክል አትሌት ሎሚ ሙለታና አትሌት ሲምቦ አለማየሁ ይወዳደራሉ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 30/2016(ኢዜአ)፦በ33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በ3000 ሜትር መሰናክል ሴቶች የፍጻሜ ውድድር አትሌት ሎሚ ሙለታና አትሌት ሲምቦ አለማየሁ ይወዳደራሉ።

በፓሪስ እየተካሄደ ያለው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ዛሬ 12ኛ ቀኑን የያዘ ሲሆን ምሽቱ 4 ሰዓት ከ14 ደቂቃ የ3000 ሜትር መሰናክል ሴቶች ፍጻሜ ውድድር ይካሄዳል።

በፍጻሜው ውድድር አትሌት ሎሚ ሙለታና አትሌት ሲምቦ አለማየሁ ኢትዮጵያን ወክለው ይሳተፋሉ።

ሐምሌ 28 ቀን 2016 ዓ.ም በተካሄደው ማጣሪያ ሎሚ አምስተኛ እንዲሁም ሲምቦ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ለፍጻሜው ማለፋቸው ይታወቃል።

አትሌት ሎሚ በማጣሪያው 9 ደቂቃ ከ10 ሴኮንድ ከ73 ማይክሮ ሴኮንድ በመግባት ከሶስት ዓመት በፊት በኔዘርላንድ ሄንግሎ ይዛው የነበረውን የርቀቱን የግል ምርጥ ሰዓቷን በ4 ሴኮንድ አሻሽላለች።

በኦሊምፒክ ሁለተኛ ተሳትፎዋን እያደረገች የምትገኘው ሎሚ በ32ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በርቀቱ ባደረገችው ማጣሪያ 10ኛ ወጥታ ለፍጻሜ አላለፈችም ነበር።

ሌላኛዋ ተወዳዳሪ አትሌት ሲምቦ በኦሊምፒክ ጨዋታዎች ስትሳተፍ የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

አትሌቷ እ.አ.አ በ2023 በጣልያን ፍሎረንስ በተካሄደው የዳይመንድ ሊግ ውድድር 9 ደቂቃ ከ00 ሴኮንድ ከ71 ማይክሮ ሴኮንድ የርቀቱ የግል ምርጥ ሰዓቷን አስመዝግባለች።

በፍጻሜው ከ11 ሀገራት የተወጣጡ 15 አትሌቶች ይወዳደራሉ። ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ አሜሪካና ጀርመን በውድድሩ በተመሳሳይ ሁለት አትሌቶችን ያሳትፋሉ።

በተያያዘም ከረፋዱ 5 ሰዓት ከ5 ደቂቃ ላይ የ1500 ሜትር ሴቶች የመጀመሪያ ዙር ማጣሪያ ይደረጋል። ጉዳፍ ፀጋይ፣ ድርቤ ወልተጂና ብርቄ ኃየሎም በማጣሪያው ላይ ይካፈላሉ።

በኦሊምፒክ ሁለተኛ ተሳትፎዋን ያደረገችው ጉዳፍ በምድብ 1 የማጣሪያ ውድድሯን ታደርጋለች።

በሚያዚያ ወር 2016 ዓ.ም በቻይና ዢያሜን በተካሄደው የዳይመንድ ሊግ ውድድር 3 ደቂቃ ከ50 ሴኮንድ ከ30 ማይክሮ ሴኮንድ አንደኛ የወጣችበት ጊዜ የርቀቱ የግል ምርጥ ሰዓቷ ሆኖ ተመዝግቧል።

አትሌት ጉዳፍ ትናንት በ5000 ሜትር ሴቶች የፍጻሜ ውድድር ዘጠነኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋ የሚታወስ ነው።

በምድብ 2 የምትገኘው ድርቤ ወልተጂ በግንቦት ወር 2016 ዓ.ም በአሜሪካ ኢውጅን በተካሄደ ውድድር 3 ደቂቃ ከ53 ሴኮንድ ከ75 ማይክሮ ሴኮንድ የርቀቱን የግል ምርጥ ሰዓቷን አስመዘግባለች።


 

ድርቤ በየካቲት ወር 2016 ዓ.ም በስኮትላንድ በተካሄደው 19ኛው የዓለም አትሌቲክስ የቤት ውስጥ ሻምፒዮና በ1500 ሜትር አምስተኛ መውጣቷ ይታወሳል።

ከአንድ ዓመት በፊት በላቲቪያ ሪጋ በተደረገው የመጀመሪያ የዓለም አትሌቲክስ የጎዳና ላይ ሩጫ ሻምፒዮና በ1 ማይል ውድድር 4 ደቂቃ ከ20 ሴኮንድ ከ98 ማይክሮ ሴኮንድ የርቀቱ የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤት ሆናለች።

ድርቤ በኦሊምፒክ ስትሳተፍ የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ ነው። በቶኪዮ በተካሄደው 32ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በ1500 ሜትር የመጀመሪያ ዙር ማጣሪያ 12ኛ ወጥታ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ አልቻለችም።

በ1500 ሜትር ማጣሪያ የምትሳተፈው ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊ አትሌት ብርቄ ኃየሎም ናት።

ብርቄ በሚያዚያ ወር 2016 ዓ.ም በቻይና ዢያሜን በተካሄደው የዳይመንድ ሊግ ውድድር 3 ደቂቃ ከ53 ሴኮንድ ከ22 ማይክሮ ሴኮንድ ሁለተኛ በመውጣት በርቀቱ ይግል ምርጥ ሰዓቷን አስመዝግባለች።

አትሌቷ በኦሊምፒክ ጨዋታዎች የመጀመሪያ ተሳትፎዋን ታደርጋለች።

በሶስት ምድብ ተከፍሎ በሚደረገው የማጣሪያ ውድድር ከየምድቡ ከእንድ እስከ ስድስት የሚወጡ አትሌቶች ለግማሽ ፍፃሜ ውድድር በቀጥታ ያልፋሉ። በየምድቡ በተመሳሳይ 15 አትሌቶች ይሳተፋሉ።

የግማሽ ፍጻሜው ሐሙስ ነሐሴ 2 ቀን 2016 ዓ.ም ከምሽቱ 2 ሰዓት ከ35 ደቂቃ ላይ ይከናወናል።

በመጀመሪያው ዙር ማጣሪያው በቀጥታ ወደ ግማሽ ፍጻሜ ያላለፉ አትሌቶች ነገ ከቀኑ 7 ሰዓት ከ45 ላይ በሁለተኛ ዙር ማጣሪያ (Repechage Round) ተካተው በድጋሚ ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ ይወዳደራሉ።

በተያያዘም ትናንት በተካሄደው የ800 ሜትር ሴቶች ፍጻሜ አትሌት ፅጌ ድጉማ ሁለተኛ በመውጣት የብር ሜዳሊያ አግኝታለች።

በ33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ በሁለት የብር ሜዳሊያዎች 49ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

አሜሪካ፣ቻይና፣ፈረንሳይ፣አውስትራሊያና ታላቋ ብሪታኒያ በሜዳሊያ ሰንጠረዡ ከአንድ እስከ አምስት ደረጃን ይዘዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም