በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በኩታ ገጠም የለማው በቆሎ ሰብል በምግብ ራስን የመቻል ጥረት ስኬታማነት ማሳያ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በኩታ ገጠም የለማው በቆሎ ሰብል በምግብ ራስን የመቻል ጥረት ስኬታማነት ማሳያ ነው
አሶሳ ፤ሐምሌ 27/2016(ኢዜአ)፦ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመኸር እርሻ በኩታ ገጠም የለማው የበቆሎ ሰብል በምግብ ራስን ለመቻል እንደአገር ለተጀመረው ጥረት ማሳያ ሊሆን እንደሚችል በመስክ ጉብኝት የተሳተፉ የግብርና ከፍተኛ አመራር አባላት ገለጹ።
በአሶሳ ከተማ ለሁለት ቀናት የተካሄደው የግብርና ሚኒስቴር፣ የክልል ግብርና ቢሮዎች እና የተጠሪ ተቋማት የጋራ ምክክር መድረክ ዛሬ ሲጠቃለል ተሳታፊዎች በአሶሳ ዞን የግብርና እንቅስቃሴዎችን ጎብኝተዋል፡፡
ተሳታፊዎቹ በአሶሳ ዞን ከጎበኟቸው መካከል 16 ሺህ 50 ሄክታር ኩታ ገጠም እርሻ፣ በክላስተር የለማ አትክልት፤ ፍራፍሬ እና የሌማት ትሩፋት ይገኙበታል፡፡
በዚህ ወቅት የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ(ዶ/ር) ፤ የክልሉ አርሶ አደሮች በቆሎ በሄክታር ከ50 እስከ 70 ኩንታል ምርት እንደሚያገኙ ከመስክ ጉብኝቱ መረዳታቸውን ገልጸዋል፡፡
ሚኒስቴሩ የክልሉ አርሶ አደሮች ያሳዩትን ተስፋ ሰጪ የኩታ ገጠም በቆሎ ሰብል እርሻን ጨምሮ በሌሎችም የመኸር እርሻ ያደረጉት ጥረት ለውጤት እንዲበቃ እንደሚደግፍ አመልክተዋል።
በተለይም የገበያ አማራጮችን ከማመቻቸት ጀምሮ አስፈላጊው ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርግ (ዶ/ር) ግርማ አስታውቀዋል፡፡
በጉብኝቱ ከተሳተፉት መካከል የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ቃልኪዳን ሽፈራው፤ በክልሉ ያለውን እምቅ አቅም በመለየት በኩታ ገጠም እርሻ የለማው የበቆሎ ሰብል የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በኩታ ገጠም የለማው ሰብል በየአካባቢው እየተስፋፉ የመጡ ለአግሮ ኢንዱትሪዎች ግብዓት ማግኘት እንደሚያስችል ገልጸዋል፡፡
ይህም ምርት እና ምርታማነትን በማሳደግ በምግብ ራስን ለመቻል የማይዋዥቅ ኢኮኖሚ ለመገንባት ለተጀመረው ጥረት የሚደግፍ እንደሆነ መመልከታቸው ጠቅሰዋል፡፡
የሲዳማ ክልል እርሻ እና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ሃላፊ አቶ ፍቅረኢየሱስ አሸናፊ በበኩላቸው ፤ የአካባቢን ምቹ ሁኔታን በመጠቀም ምርታማነትን ማሳደግ የሲዳማ ክልልም እንደሃገር የሚከተለው አቅጣጫ ነው ብለዋል፡፡
ይህም በግብርና እንቅስቃሴ ውስጥ ወሳኝ ነው ያሉት ተሳታፊው፤ በክልሉ ባደረግነው የኩታ ገጠም የበቆሎ እርሻ ጉብኝት ይህንን በተጨባጭ ያሳየ ውጤት ነው ብለዋል፡፡
ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አርሶ አደሮች ያሳዩት ውጤት በሁሉም አካባቢዎች በስፋት በማከናወን በምግብ ራስን እንደሚቻል ያመላከተ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ኩታ ገጠም እርሻ የምርት ብክነት ከማስቀረት ባለፈ ምርታማነትን እንደሚያመጣ የተናገሩት ደግሞ በመስክ ጉብኝቱ የተሳተፉት ሌላው ከፍተኛ አመራር የኢትዮጵያ ብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መለሰ ማርዬ ናቸው፡፡
የክልሉ አርሶ አደሮች በኩታ ገጠም ያለሙት የበቆሎ ሰብል አሁን ያለበት ተስፋ ሰጪ ደረጃ ከግብርና ባለሙያዎች በመቀናጀት እና ሜካናይዝድ እርሻ መጠቀማቸው እንደሆነ እንደሚሳይ አመልክተዋል፡፡
አገሪቱም በግብርናው ዘርፍ ተስፋ እንዳላት በተግባር ተመልክቻለሁ ብለዋል፡፡