ኮርፖሬሽኑ ገበያን ለማረጋጋት የሚያግዙ የፍጆታ ምርቶች ቀጥታ ከአርሶ አደሩና ከውጪ ገበያ ገዝቶ እያቀረበ መሆኑን ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ኮርፖሬሽኑ ገበያን ለማረጋጋት የሚያግዙ የፍጆታ ምርቶች ቀጥታ ከአርሶ አደሩና ከውጪ ገበያ ገዝቶ እያቀረበ መሆኑን ገለጸ
አዳማ፤ ሐሞሌ 27/2016 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽ ገበያን ለማረጋጋት የሚያግዙ የፍጆታ ምርቶች ቀጥታ ከአርሶ አደሩና ከውጪ ገበያ ገዝቶ እያቀረበ መሆኑን ገለጸ።
የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አቻ ደምሴ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ ኮርፖሬሽኑ የተለያዩ ምርቶችን ገዝቶ ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረበ ነው።
በዚሁ መሰረት ኮርፖሬሽኑ ገበያን ለማረጋጋት የሚያግዙ "የፍጆታ ምርቶችን ቀጥታ ከአርሶ አደሩና ከውጪ ገበያ ገዝቶ እያቀረበ ነው" ብለዋል።
ከአገር ውስጥ ገበያ ላይ የጤፍ፣ ስንዴ፣ ቦቆሎ፣ የዳቦ ዱቄትና ሌሎች የግብርና ምርቶች ተገዝተው በኮርፖሬሽኑ የግብይት ማዕከላት በኩል ለህብረተሰቡ እየቀረቡ መሆኑን ተናግረዋል።
ከአገር ውጪም የምግብ ዘይት በስፋት እየተገዛ መሆኑን ገልጸው፤ ይህም ያለውን የገበያ ክፍተት ለመሙላት የሚያግዝ መሆኑን ነው የተናገሩት።
በተጨማሪም ለመጪው የትምህርት ዘመን የሚያገለግሉ የመማሪያ ደብተሮች ተገዝተው ወደ አገር ውስጥ እየገቡ መሆኑን አስረድተዋል።
የኮርፖሬሽኑ የቡናና እህል ግብይት ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ገመቺስ መላኩ በበኩላቸው፤ ከአንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ኩንታል በላይ ጤፍ፣ ስንዴ፣ ቦቆሎ፣ የዳቦ ዱቄት፣ ስኳርና ሌሎች ምርቶች ተገዝተው በኮርፖሬሽኑ የግብይት ማዕከላት በኩል ለግብይት ቀርበዋል ብለዋል።
በተጨማሪም አትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች በስፋት ተገዝቶ እየቀረበ መሆኑን ገልጸው፤ የገበያ የአቅርቦት ጉድለት በሚኖርባቸው ቦታዎች ላይ ጭምር ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህ ወቅትም ኮርፖሬሽኑ በቂ የፍጆታ ምርቶች ክምችት በየማዕከላቱ እንዳለው አረጋግጠዋል።
ኮርፖሬሽኑ በተለያዩ ክልሎች 28 የግብይት ማዕከላት ያሉት ሲሆን፤ ከክልሉ ንግድ ተቋማት ጋርም በቅርበት እየሰራ መሆኑ ተገልጿል።
የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ትላንት እንዳመለከተው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ ትግበራን ተከትሎ በመሰረታዊ የምግብ ሸቀጦች ላይ የአቅርቦትና የዋጋ ጭማሪ እንዳይከሰት መንግስት በቂ ዝግጅት ማድረጉን ገልጿል።
የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉና ምርትን በማከማቸት እጥረት እንዲፈጠር በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ ጥብቅ እርምጃ እየተወሰደ እንደሆነም ተናግረዋል።