ቀጥታ፡

ባንኩ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የፋይናንስ ተቋም እንዲሆን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በምርምርና ቴክኖሎጂ ድጋፍ ያደርጋል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 26/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የፋይናንስ ተቋም እንዲሆን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ድጋፍ እንደሚያደርግ የዩኒቨርሲቲው ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር ) ገለጹ።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በእውቀት፣ በምርምርና በፋይናንስ ጉዳዮች በጋራ ለመስራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ዛሬ ተፈራርሟል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፣ ዩኒቨርሲቲው ራስ ገዝ መሆኑን ተከትሎ የአምስት አመት ስትራቴጂ እቅድ አውጥቶ እየሰራ ነው ።

በዚህም ዩኒቨርሲቲው ለሀገራዊ የእውቅት ሽግግር ፍላጎቶች በጥናትና በምርምር፣ በማማከርና በቴክኖሎጂ የተደገፈ ምላሽ ለመስጠት እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

የዛሬው ስምምነት በባንክ ኢንዱስትሪው ረጅም ዓመት ሲሰራ የቆየ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በሰው ኃይል ልማት፣ በጥናትና ምርምር፣ በፋይናንስ፣ በማማከርና በቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ በጋራ ለመስራት የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል።

የሁለቱ አንጋፋ ተቋማት በጋራ መስራትም ኢትዮጵያ የምትፈልገውን ለውጥ ለማምጣት ትልቅ እርምጃ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የፋይናንስ ተቋም እንዲሆን በስምምነቱ ማዕቀፍ መሰረት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የበኩሉን እገዛ ያደርጋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት ተወካይ አቶ ኤፍሬም መኩሪያ በበኩላቸው፣ ከዚህ ቀደም በነበረው ተሞክሮ የባንክ ዘርፉ እምብዛም በምርምር የተደገፈ አለመሆኑን ገልጸዋል።

የባንኩ አገልግሎት በምርምርና ቴክኖሎጂ ይበልጥ እንዲደገፍ ይህ ስምምነት ወሳኝ ስለመሆኑም ገልጸዋል።

በዚህም ዩኒቨርሲቲው፣ በዘርፉ በሰለጠነ የሰው ኃይል፣ በቴክኖሎጂና የዲጂታል ሽግግር እንዲሁም በምርምርና በማማከር ላይ በጋራ መስራት ለቀጣይ የባንኩ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም