ከማዕድን ዘርፍ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው - ኢንጅነር ሐብታሙ ተገኝ - ኢዜአ አማርኛ
ከማዕድን ዘርፍ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው - ኢንጅነር ሐብታሙ ተገኝ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 26/2016 (ኢዜአ)፦ ከማዕድን ዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የማዕድን ሚኒስትር ኢንጅነር ሐብታሙ ተገኝ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ጂኦ-ሳይንስ እና የማዕድን ምህንድስና ማህበር "የጅኦ-ሳይንስ እና የማዕድን ምህንድስና ዘርፍ ለማህበረ-ኢኮኖሚ ልማት ያላቸው ሚና" በሚል ሃሳብ 9ኛውን ጉባኤ ዛሬ ማካሄድ ጀምሯል።
በጉባኤው መክፈቻ የተገኙት የማዕድን ሚኒስትር ኢንጅነር ሐብታሙ ተገኝ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የተለያዩ የማዕድን ሐብቶች ቢኖሯትም በሚፈለገው ልክ ጥቅም ላይ ማዋል አልቻለችም፡፡
ከዚህ ቀደም ለዘርፉ ትኩረት ባለመሰጠቱ ኢንቨስትመንቶችና የቴክኖሎጂ ግብዓቶች በበቂ ሁኔታ አለመቅረባቸውን ጠቁመዋል፡፡
ዘርፉን ወደፊት ሊያራምዱ የሚችሉ የስትራቴጂ እና የፖሊሲ ማዕቀፎች እንዳልነበሩም እንዲሁ፡፡
ከለውጡ ወዲህ ግን መንግስት የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለማሳደግ እንደ አንድ ዋና የልማት ምሰሶ አድርጎ እየሰራበት እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
እስካሁን በተከናወኑ ስራዎች አገሪቱ ያላትን የማዕድን ጸጋዎች ለይቶ ጥቅም ላይ ከማዋል አንጻር አበረታች ጅምሮች ቢኖሩም፤ ካለው ሰፊ ሀብት አኳያ ግን የሚቀር ስራ መኖሩን አስታውቀዋል፡፡
በዚህም ብረትን ጨምሮ የተለያዩ ምርቶችን ከውጪ ለማስገባት በርካታ ዶላሮች ወጪ እንደሚደረጉ ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት የአገር ውስጥ የማዕድን ጥሬ እቃዎችን በመጠቀም ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ምርቶች ለመተካትና የማዕድን ምርቶችን እሴት ጨምሮ ወደ ውጪ በመላክ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ችግሩን ለመቅረፍ ተቋሙን መልሶ የማደራጀት፣ ብቁ ባለሙያዎችን የማፍራት፣ ዘመናዊ አሰራር መፍጠርና በጥናት ላይ በተመሰረተ ሂደት ግብዓት የመጠቀም ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በዚህ ሒደት የባለድርሻ አካላት ትብብር የማይተካ ሚና ያለው መሆኑን ገልጸው፤ ለዚህም ሚኒስቴሩ ምቹ ሁኔታዎችን የሚፈጥር መሆኑን ነው ያስታወቁት ፡፡
በዚህ በጀት አመት ለሰው ሀይል ግንባታና ለሌሎች ዘርፉን ለሚያሳድጉ ጉዳዮች ከፍተኛ በጀት መያዙን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ጂኦ-ሳይንስና የማዕድን ምህንድስና ማህበር ፕሬዘዳንት ዶክተር ታረቀኝ ታደሰ በበኩላቸው፤ ማህበሩ በዘርፉ ያሉ ክፍተቶችን ለመሙላት ከ 30 አመታት በፊት መመስረቱን ተናግረዋል።
በነዚህ አመታት በገጠሙት የተለያዩ ተግዳሮቶች ማህበሩ የተመሰረተበትን አላማ በሚፈለገው ልክ ሳያሳካ መቆየቱን አመላክተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት መንግስት ዘርፉን ለማዘመንና ለማሳደግ ያሳየውን ቁርጠኝነት ተከትሎ ከ13 አመታት በኋላ 9ኛ ጉባዔውን ለማካሄድ መቻሉን ተናግረዋል ፡፡
በቀጣይ ኢትዮጵያ ከማዕድን ሃብቷ በሚፈለገው መጠን ተጠቃሚ እንድትሆን ማህበሩ ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ ሃሳቦችን በማቅረብ፣ ጥናትና ምርምሮችን በመስራትና የአቅም ግንባታ ድጋፍ በማድረግ የበኩሉን እንደሚወጣ አረጋግጠዋል፡፡
ጉባዔው ነገ እንደሚጠናቀቅ ከወጣው መርኃ ግብር መረዳት ተችሏል፡፡