ለኢትዮጵያ የሚበጁና የሚያግባቡ ሃሳቦችን በማዋጣት ዘላቂ ሰላም እውን እንዲሆን ሁሉም ሚናውን ሊወጣ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ለኢትዮጵያ የሚበጁና የሚያግባቡ ሃሳቦችን በማዋጣት ዘላቂ ሰላም እውን እንዲሆን ሁሉም ሚናውን ሊወጣ ይገባል
ጋምቤላ፤ ሐምሌ 26/2016 (ኢዜአ)፡-ለኢትዮጵያ የሚበጁና የሚያግባቡ ሃሳቦችን በማዋጣት ዘላቂ ሰላምን እውን ለማድረግ ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር መላኩ ወልደማሪያም አስገነዘቡ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በጋምቤላ ክልል ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ከተወከሉ ተመራጮች፣ ባለድርሻ አካላት ጋር እያካሄደ ያለው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት እንደቀጠለ ነው።
ኮሚሽነር መላኩ ወልደማሪያም በክልሉ እየተካሄደ ባለው የአጀንዳ ማሰባሰብ መርሃ ግብር ላይ እንደገለጹት፤ የአገርን ሉዓላዊነትና አንድነት ማስቀጠልና ማጽናት የሚቻለው ዘላቂ ሰላም ሲሰፍን ነው ።
ከግለኝነትና ከማያግባቡ አስተሳሰቦች በመውጣት ለአገር ዘላቂ ሰላም እውን መሆን ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
"ሁላችንም ለሁላችን እናስፈልጋለን" ያሉት ኮሚሽነሩ፤ ይህን ታሳቢ በማድረግ ለቀጣይ ትውልድ መልካም አሻራ ጥሎ ለማለፍ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
በአጀንዳ ማሰባሰቡ የውይይት መድረክ የተገኙ ተሳታፊዎችም በቆይታቸው ለአገር የሚበጁና የሚያግባቡ ሃሳቦችን በማዋጣት ረገድ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ በጋምቤላ ክልል ዛሬ አስቀጥሎት ባለው የአጀንዳ ማሰበሳብ መድረክ ታዋቂ ግለሰቦች፣ የመንግስት ተቋማት ተወካዮች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የማህበራት ተወካዮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
ተሳታዎቹ በቡድን ተከፍለው የአጀንዳ ማሰበሳብ ስራቸውን አካሂደዋል።