በሲዳማ ክልል በንግድ ልውውጥ ወቅት ህገ ወጥ ተግባር የፈጸሙ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ እየተወሰደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሲዳማ ክልል በንግድ ልውውጥ ወቅት ህገ ወጥ ተግባር የፈጸሙ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ እየተወሰደ ነው
ሀዋሳ ፤ ሐምሌ 26/2016(ኢዜአ)፦ በሲዳማ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች በንግድ ልውውጥ ወቅት ህገ ወጥ ተግባር የፈጸሙ ነጋዴዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን ክልሉ አስታወቀ።
የክልሉ ህገ ወጥ ንግድ መከላከል ግብረ ሃይል በወቅታዊ የንግድ እንቅስቃሴ ላይ ያተኮረ ምክክር በሀዋሳ አካሂዷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ፖሊሲ ላይ ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት፤ ለሕግ አስፈጻሚ አካላት የለውጥ ሥራውን ባልተገባ ሕገ ወጥ መንገድ ለመጠቀም በሚፈልጉ ስግብግብ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ እንዲወስዱ ኃላፊነት መሰጠቱን ገልጸዋል።
በለውጥ ሥራው ላይ ያልተገባ ዓይነት የንግድ ስርዓት መፍጠር እንደማይፈቀድም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በአጽንኦት መግለጻቸው ይታወሳል።
በየደረጃው ያሉ የመንግስት አካላትም በግብይት ወቅት ያልተገባ ድርጊት በሚፈጽሙ እና ሸቀጦችን በሚደብቁ የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ እየወሰዱ ይገኛሉ።
የሲዳማ ክልል ህገ ወጥ ንግድ መከላከል ግብረ ሃይል ሰብሳቢና የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ በየነ በራሳ እንደገለጹት፤ የፖሊሲ ትግበራውን ተከትሎ በግብይቱ ወቅት ህገ ወጥ ተግባር የሚፈጽሙ፣ ምርት የሚደብቁና ያለአግባብ የሚያከማቹትን ለመከላከል የተቀናጀ ስራ እየተሰራ ነው።
ከክልል ጀምሮ እስከታችኛው የመንግስት መዋቅር ድረስ የቁጥጥር ግብረ ኃይል በማቋቋም ጥብቅ ክትትል እየተደረገ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።
በዚህም በዞን፣ በወረዳና በከተሞች ላይ በተደረገው ክትትል ህገ ወጥ የግብይት እንቅስቃሴዎች መታየታቸው መረጋገጡን አውስተዋል።
በዚህ ረገድ በጥቂት ቀናት ውስጥ ብቻ ወደ 250 በሚሆኑ የንግድ ተቋማት ላይ ክትትል መደረጉን አመልክተው፤ ጥፋተኛ ሆነው ለተገኙ 40 ተቋማት ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን አስታውቀዋል።
ሰባት በሚሆኑ የንግድ ተቋማት ላይ ደግሞ የማሸግ እርምጃ እንደተወሰደባቸው ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውቀዋል።
በቀጣይም በክልሉ በህገ ወጥ ነጋዴዎች ላይ የሚወሰደው ህጋዊ እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
ህብረተሰቡ ህገ ወጥ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ነጋዴዎች ሲያጋጥመው ለሚመለከተው የህግ አካላት በማሳወቅ የበኩሉን አስተዋፅኦ እንዲያደረግ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል።