የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በጋራ ለመስራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በጋራ ለመስራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 26/2016(ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በእውቀትና በፋይናንስ የምርምር ስራዎች በጋራ ለመስራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።
ስምምነቱን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት ተወካይ አቶ ኤፍሬም መኩሪያ ፈርመውታል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው ራስ ገዝ መሆኑን ተከትሎ የአምስት አመት ስትራቴጂ እቅድ አውጥቶ እየሰራ ነው ።
ዩኒቨርሲቲው በቀጣይ ለሚያከናውናቸው የእውቀት፣ የጥናትና ምርምር ስራዎች እንዲሁም ሌሎችም ተግባራት ከፋይናንስ ተቋማት ጋር መስራት የሚጠበቅ መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመጪው ጊዜያት ለሚያከናውናቸው ስራዎች ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችለውን ስምምነት ማድረጉን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት ተወካይ አቶ ኤፍሬም መኩሪያ በበኩላቸው፣ ዩኒቨርሲቲው ለሀገር የሚያበረክታቸው ሰፊ የእውቀትና የምርምር ስራ ለመደገፍ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በጋራ ለመስራት ቁርጠኛ ነው ብለዋል።
እንዲሁም በስምምነቱ ዩኒቨርሲቲው በሰው ሃይል ልማት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር በምርምርና የምክር አገልግሎት ለባንኩ የሚሰጥባቸው አግባብ የሚጠናከር መሆኑን ገልጸዋል።