ቀጥታ፡

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠናን ጨምሮ በዓለም አቀፍ ገበያ ተጠቃሚ እንድትሆን ያደርጋል- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 26/2016(ኢዜአ)፦የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ተዘግቶ የቆየውን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ክፍት በማድረግ የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠናን ጨምሮ በዓለም አቀፍ ገበያ ተጠቃሚ እንድንሆን ያደርገናል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን በተመለከተ ትናንት በሰጡት ማብራሪያ፤ ማሻሻያውን  በቁንጽል ሳይሆን በምልዐት መመልከት  እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ማሻሻያው አገራዊ ለውጡን ተከትሎ እየተተገበረ ያለውን በመደመር እሳቤ የልማት ጸንሰ ሃሳብ መርሆችን መሰረት ያደረገ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ 

በአገራዊ ለውጡ ማግስት መንግስት ከወሰናቸው ውሳኔዎች መካከል አንደኛው የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ  ለግሉ ዘርፉ ተሳትፎ ክፍት ማድረግ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡

ከዛ በኋላ ባሉ ሂደቶችም በተለይ በመጀመሪያ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ አማካኝነት በተወሰነ መልኩ ኢኮኖሚውን ለግሉ ሴክተር ተሳትፎ ነጻ የማድረግ ስራ መከናወኑን አንስተው፤ ከዚህ አኳያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው አዲስ ጉዳይ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

የመጀመሪያው የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያም ፈተናዎችን በመቋቋም በርካታ ውጤቶች መመዝገባቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በአፍሪካ ግዙፍ ኢኮኖሚ ከገነቡ አገራት መካካል የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ብቻ በበርካታ ጉዳዮች ዝግ እንደነበር የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አሁን ላይ ባለው ነባራዊ ሁኔታ በዚህ መንገድ ኢኮኖሚውን አስቀጥሎ ውጤታማ ማድረግ አይቻልም ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የረሷን ኢኮኖሚ ዘግታ የአፍሪካ የንግድ ቀጠናን ጨምሮ በዓለም አቀፍ ገበያ ተጠቃሚ መሆን እንደማትችልም ነው አጽኖት ሰጥተው ያብራሩት፡፡

ኢትዮጵያ በተለይ በአህጉር አቀፍ ደረጃ ተገባራዊ በሚደረገው የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ተጠቃሚ ለመሆን የተዘጋው ኢኮኖሚ ክፍት መደረግ እንዳለበት ገልጸው፤ ማሻሻያውም ይህን ተግባራዊ የሚያደርግ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ማሻሻያው ከዚህ በፊት የተመዘገቡ ስኬቶችን በማስቀጠልና አዳዲስ እድሎችን በመፍጠር የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ የተጀመሩ ጥረቶችን ለማሳከት እንደሚያግዝም አንዲሁ፡፡

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም