4ኛው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ለልማት ቅድመ ጉባኤ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎችን በብቃት የማስተናገድ አቅም እንዳላት ያሳየ ነው - ኢዜአ አማርኛ
4ኛው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ለልማት ቅድመ ጉባኤ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎችን በብቃት የማስተናገድ አቅም እንዳላት ያሳየ ነው
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 26/2016(ኢዜአ)፦በአዲስ አበባ የተካሄደው 4ኛው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ለልማት ቅድመ ጉባኤ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎችን በብቃት የማስተናገድ አቅም እንዳላት ያሳየ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብዩ ተድላ በወቅታዊ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲና የውጭ ግንኙነት ላይ ሳምንታዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
ቃል አቀባዩ፤ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ለልማት ቅድመ ጉባኤ የዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት የሚያስፈልገውን የፋይናንስ አቅርቦት ለማፈላለግ ውይይት የተደረገበት ነው ብለዋል።
በኮንፍረንሱ ሚኒስትሮችን ጨምሮ ከአንድ ሺህ በላይ ተሳታፊዎች የተገኙበት ሲሆን ጉባኤው በአዲስ አበባ መካሄዱ ኢትዮጵያ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን ማስተናገድ እንደምትችል ያሳየ ነው ብለዋል።
ከኮንፍረንሱ ባለፈ 12 የጎንዮሽ ውይይቶች መደረጋቸውን ጠቅሰው፣ በሰላም፣ በጸጥታና በልማት ላይ የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ያስረዳንበት መድረክ ነው ብለዋል።
በዲፕሎማሲ፣ ቱሪዝምና ገጽታ ግንባታ ዘርፍ ውጤት የተገኘበት ኮንፍረስ እንደነበርም አስረድተዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ስምሪት የተሰጣቸው 24 አዳዲስ አምባሳደሮች የሀገራቸውን ብሄራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ በፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ፊት ቃል መግባታቸውን አስረድተዋል።
አዳዲስ ተሿሚ አምባሳደሮች ያዳበሩትን ልምድ ተጠቅመው በትጋት እንዲሰሩ ሀላፊነት እንደተሰጣቸውም እንዲሁ።
ከዚህም ባለፈ በቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የተመራ የልዑካን ቡድን ነገ አዲስ አበባ ይገባል ብለዋል።