የተለያዩ ተቋማት በገዜ ጎፋ ወረዳ በመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች የሚውል ድጋፍ አደረጉ - ኢዜአ አማርኛ
የተለያዩ ተቋማት በገዜ ጎፋ ወረዳ በመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች የሚውል ድጋፍ አደረጉ
ሳውላ፤ሐምሌ 26/2016 (ኢዜአ)፡-የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትና የብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ በደረሰ የመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች ከ9 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ አደረጉ ።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ድጋፉን ዛሬ ባስረከቡበት ወቅት እንዳሉት ሚኒስቴሩ አደጋው ከደረሰበት ጊዜ አንስቶ ሀዘኑን ሲገልጽ ቆይቷል።
በዛሬው ዕለት ሚኒስቴሩ ከብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ ጋር በመሆን 2 ሚሊዮን ብር በጥሬ ገንዘብ እና 2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።
በቀጣይም ተጎጂዎች በዘላቂነት እስኪቋቋሙ ድረስ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የ5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ሽፈራው ተሊላ ገልጸዋል።
አገልግሎቱ ተጎጂዎችን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት ሁሉ የሚጠበቅበትን እንደሚወጣ አረጋግጠዋል።
የብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ ምክትል ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መስከረም አበበ በበኩላቸው የሊጉ አባላት የጀመሩትን ድጋፍ በቀጣይም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
ድጋፉን የተረከቡት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የግብርናና ገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የውሀ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ሀላፊ ኢንጅነር አክሊሉ አዳኝ ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።