የሉሲ ቅሪተ አካል 50ኛ ዓመት መታሰቢያ መርሃ ግብር ከሳይንሳዊ ፋይዳም የለቀ ሀገራዊ ጠቀሜታ አለው - ኢዜአ አማርኛ
የሉሲ ቅሪተ አካል 50ኛ ዓመት መታሰቢያ መርሃ ግብር ከሳይንሳዊ ፋይዳም የለቀ ሀገራዊ ጠቀሜታ አለው
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 25/2016(ኢዜአ)፦የሉሲ ቅሪተ አካል 50ኛ ዓመት መታሰቢያ መርሐ ግብሮች ከሳይንሳዊ ፋይዳቸው ባሻገር የኢትዮጵያን ገጽታ ለመገንባትና የቱሪዝም ሀብቶችን ለዓለም ለማስተዋወቅ የላቀ ፋይዳ ያላቸው መሆኑን የአሪዞና ስቴት ዩኒቨርሲቲ የሰው ዘር አመጣጥ ምርምር ተቋም ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ዮሐንስ ኃይለሥላሴ ተናገሩ፡፡
ሉሲ ወይም ድንቅነሽ የተሰኘችው ቀደምት የሰው ዘር ቅሪተ አካል በኢትዮጵያ ከተገኘች ግማሽ ምዕተ ዓመት አስቆጥራለች፡፡
በዚህም የሉሲ ቅሪተ አካል የተገኘችበትን 50ኛ ዓመት ለመዘከር ባሳለፍነው የፈረንጆቹ አዲስ ዓመት ከወርኃ ጥር ጀምሮ ዓመቱ ''የሉሲ ዓመት'' በሚል ተሰይሞ በተለያዩ መርሐ ግብራት እየተዘከረ ይገኛል፡፡
የዝክረ-ሉሲ 50ኛ ዓመት መታሰቢያ አካል የሆነ ከ34 ሀገራት ዕውቅ የዘርፉ ተመራማሪዎች የታደሙበት ዘጠነኛው የምስራቅ አፍሪካ ፓሌዮአንትሮፖሎጂና ፓሌዮንቶሎጂ ጥናት ጉባዔ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡
ከጉባዔው ጎን ለጎንም በአድዋ ድል መታሰቢያ የፎቶ ዐውደ ርዕይ የተከፈተ ሲሆን በዛሬው ዕለትም የጉባዔ ተሳታፊዎች በአዲስ አበባ የሚገኙ የተለያዩ ታሪካዊ ስፍራዎችን ተመልክተዋል፡፡
ከጉባዔው ታሳታፊዎች መካከል በቅድመ ሰው ዘር አመጣጥ (ፓሌዮአንትሮፖሎጂ) ዘርፍ ኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት የሚያጠናው የአሜሪካ የአሪዞና ስቴት ዩኒቨርሲቲ የሰው ዘር አመጣጥ ምርምር ተቋም ምሁራን ይገኙበታል፡፡
የተቋሙ ዳይሬክተር ዕውቁ የዘርፉ ተመራማሪ ኢትዮጵያዊ ፕሮፌሰር ዮሐንስ ኃይለሥላሴ፤ የሉሲ ቅሪተ-አካል 50ኛ ዓመት መታሰቢያ እስከ ቀጣይ ዓመት ኅዳር ወር በተለያዩ ዝግጅቶች መዘከሩ ትልቅ ፋይዳ አለው ብለዋል።
ከሰሞኑ የተካሄደው የሉሲ ቅሪተ አካል መታሰቢያ አካል የሆነው ጉባዔ እና ዐውደ ርዕይ ከ34 ሀገራት የተውጣጡ ከ240 በላይ የቅድመ ሰው ዘር ተመራማሪዎች የታደሙበት ስኬታማ ጉባዔ እንደነበርም አንስተዋል።
ጉባዔው የሰው ዘር መገኛ በሆነችው ኢትዮጵያ መደረጉ ልዩ እንደሚያደርገው ገልጸው፤ የጉባዔው ተሳተፋዎችም ከዚህ በፊት ከተደረጉ ጉባዔዎች በተለዬ ድምቀትና ከፍታ የተከበረ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በዛሬው ዕለትም ተመራማሪዎቹ የኢትዮጵያን ታሪክና ቅርስ ሀብት እንዲመለከቱ በአድዋ ድል መታሰቢያ፣ በብሔራዊ ቤተ መዘከር እና በአንድነት ፓርክ ጉብኝት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
ጎብኚዎቹ በተመለከቱት ስፍራ እና ታሪካዊ ቅርሶች በእጅጉ መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡
ጉባዔው እና የምሁራኑ ጎብኝት ከሳይንሳዊ ፋይዳው ባሻገር ኢትዮጵያን ገፅታ ለመገንባት ብሎም የቱሪዝም ሀብቶችን ለተቀረው ዓለም ለማስዋወቅ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳላቸው ነው ፕሮፌሰሩ የተናገሩት፡፡
የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አበባው አያሌው፤ ሰሞነኛውን ጉባዔ ጨምሮ የሉሲ ቅሪተ አካል መታሰቢያ ዝግጅቶች ዘርፈ ብዙ ፋይዳ እንዳላቸው ጠቅሰዋል፡፡
ኢትዮጵያ በሰው ዘር ቅሪተ አካል ምንጭነቷ የሚስተካከላት እንደሌለ ገልፀዋል፡፡
የሉሲን ቅሪተ አካል ያገኙት ፕሮፌሰር ዶናልድ ጆንሰንን ጨምሮ የዕውቅና ጉምቱ የዘርፉ ተመራማሪዎች ጉብኝት ለኢትዮጵያ ገጸታ ግንባታ አይተኬ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ቅርስና ታሪኳን በራሷ አደራጅታ ለጎብኚዎች ክፍት ያደረገችበት መንገድ ለምሁራኑ ያልጠበቁትና ትልቅ ደስታ የፈጠረላቸው አጋጣሚ መሆኑን አንስተዋል፡፡
''በቱሪዝም ዘርፍ አዲስ ምዕራፍ ተከፍቷል'' ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ በተፈጥሮ፣ በታሪክ እና በባህል ቅርሶችን ያቀናጁ የቱሪስት መዳረሻዎች በስፋት እየለሙ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም በዓለም ላይ ተዕጽኖ ፈጣሪ የዘርፉ ተመራማሪዎች በምርምር ኢትዮጵያን ከማስተዋወቃቸው በተጨማሪ እየተሰሩ ያሉ የቱሪዝም ሀብቶችን ይበልጥ ለማስተዋወቅ እንደሚያግዝ ገልጸዋል፡፡
የ3 ነጥብ 2 ሚሊየን ዓመት ዕድሜ ያላት የሰው ልጅ ቅሪተ-አካሏ ሉሲ ወይም ድንቅነሽ በአውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር ኅዳር 24 ቀን 1974 በአፋር ክልል ''ሐዳር" የተባለ ስፍራ ነበር የተገኘችው፡፡
በዚህም ዘንድሮ የሉሲ ቅሪተ አካል መገኘት 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ መታሳቢያ እየተዘከረ ይገኛል።