በዲላ ከተማ በተያዘው ክረምት 17 የአቅመ ደካማ ቤቶች ግንባታና ጥገና ተከናውኗል - ኢዜአ አማርኛ
በዲላ ከተማ በተያዘው ክረምት 17 የአቅመ ደካማ ቤቶች ግንባታና ጥገና ተከናውኗል
ዲላ ፤ ሐምሌ 25/2016(ኢዜአ)፦በዲላ ከተማ በተያዘው ክረምት 17 የአቅመ ደካማ ቤቶች ግንባታና ጥገና መከናወኑን የከተማው ወጣቶችና ስፖርት ጽህፈት ቤት ገለጸ።
በጉሙሩክ ኮሚሽን የሐዋሳ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የጪጩ መቆጣጠሪያ ጣብያ በዲላ ከተማ የአቅመ ደካማ ቤት ግንባታ አስጀመረ።
በዚሁ ጊዜ የዲላ ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ መላኩ አየለ፣ በከተማው ዘርፍ ብዙ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አንስተዋል።
በተለይ በክረምት ወራት የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማስተባበር ለአቅመ ደካሞች ከ400 በላይ የቤቶች ግንባታና ጥገና ለማከናወን ታቅዶ እስካሁን 17 ቤቶች ግንባታና ጥገና መከናወኑን ጠቅሰዋል።
የጉሙሩክ መቆጣጠሪያ ጣብያው ሀላፊዎችና ሰራተኞች በአካባቢው ከፀጥታ ከማስከበር ተግባር ጎን ለጎን በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ለሚያደርጉት ተሳትፎ ምስጋና አቅርበዋል።
የጉሙሩክ መቆጣጠሪያ ጣብያው የአስተባባሪ ኮማንደር ቅባቱ ምራኒ በበኩላቸው ጣብያው ከሚያከናውነው የኮንትሮባንድ መከላከልና መቆጣጠር ተግባር ጎን ለጎን በልዩ ልዩ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ እየተሳተፈ ነው።
ከዚህ ውስጥ አንዱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሲሆን በዛሬው ዕለትም በዲላ ከተማ የአንድን አቅመ ደካማ ቤት ግንባታ በማስጀመር የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መጀመራቸውን ተናግረዋል።
ይህም በሀገር አቀፍ ደረጃ የአቅመ ደካሞችን ቤት በመገንባትና በማደስ ኑሯቸውን ለማሻሻል የሚደረገውን ጥረት የሚያጠናክር መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የጣቢያው ሀላፊና ሰራተኞች ከጉልበትና የግንባታ ግብዓቶች በተጨማሪ ከ75 ሺህ ብር በላይ ወጭ ማድረጋቸውን ጠቅሰው መሰል የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በቀጣይ በተለያዩ አካባቢዎች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
ባጋጠማቸው የአካል ጉዳት ምክንያት ህይወታቸውን በአስቸጋሪ ሁኔታ ሲመሩ መቆየታቸውን የገለፁት ደግሞ የቤት ግንባታ የተጀመረላቸው የከተማው ነዋሪ ወይዘሮ አዳነች አራርሶ ናቸው።
በተለይም የክረምት ወራት ዝናብና ብርድ መቋቋም በእጅጉ አዳጋች ሆኖባቸው እንደነበርም አስረድተዋል።
በአሁኑ ወቅት የቤታቸው ግንባታ መጀመሩ በእጅጉ እንዳስደሰታቸው የገለፁት ወይዘሮ አዳነች ተግባሩ ለቀጣይ ጊዜ ህይወታቸው መቃናት አስተዋጽኦው ከፍተኛ መሆኑን ገልፀዋል።
በአስቸጋሪ ጊዜ ለደረሱላቸው በጎ ፈቃደኞች ምስጋና አቅርበዋል።