የካንሰር በሽታዎች የህክምና መመሪያ በመቅረጽ የበሽታውን ቅድመ-ልየታና ህክምና አገልግሎት ለማዳረስ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የካንሰር በሽታዎች የህክምና መመሪያ በመቅረጽ የበሽታውን ቅድመ-ልየታና ህክምና አገልግሎት ለማዳረስ እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 25/2016(ኢዜአ)፡- የካንሰር በሽታዎች የህክምና መመሪያ በመቅረጽ የበሽታውን ቅድመ-ልየታና ህክምና አገልግሎት ለማዳረስ እየተሰራ እንደሚገኝ የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የዓለም የሳንባ ካንሰር ቀን በየአመቱ ሐምሌ 25 ቀን መከበር ከጀመረ 13 አመት ያስቆጠረ ቢሆንም በኢትዮጵያ ቀኑ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ተከብሮ ውሏል፡፡
ቀኑ የሚከበረው በዋናነት በኢትዮጵያ ስላለው የሳንባ ካንሰር ገጽታ፣ የህከምና ሁኔታና ተግዳሮቶች ግንዛቤ ለማስጨበጥ ነው፡፡
የሳንባ ካንሰር በአለማቀፍ ደረጃ በስፋት ከሚታወቁ የካንሰር አይነቶች አንዱ ሲሆን በገዳይነቱ ደግሞ በቀዳሚነት ይቀመጣል።
በጤና ሚኒስቴር የካንሰር መከላከልና መቆጣጠር አማካሪ ዶክተር ክኑዝ አብደላ ሚኒስቴሩ ለሳንባ ካንሰርና ሌሎች የካንሰር በሽታዎች የህክምና መመሪያ በመቅረጽ የበሽታውን ቅድመ-ልየታና ህክምና አገልግሎት ለማዳረስ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
በዚህም የካንሰር ህክምና የሚሰጡ ተቋማትን ቁጥር በመጨመር 30 በሚሆኑ ሆስፒታሎች ውስጥ ህክምናውን ለመስጠት መቻሉን በመጥቀስ የካንሰር የጨረር ህክምና የሚሰጥበትን የራዲዮቴራፒ አገልግሎት ከአንድ ተቋም ወደ ሰባት ማሳደግ መቻሉን ገልጸዋል፡፡
በካንሰር ህክምና ላይ ያለውን የባለሙያ እጥረት ለመቅረፍ የክሊኒካል ኦንኮሎጂስች ቁጥር ከነበረበት አራት ወደ 50 ማሳደግ መቻሉንም ጠቅሰዋል ፡፡
የጤና ሚኒስቴር የካንሰር መድኃኒት አቅርቦትን ተደራሽ ለማድረግ 60 በመቶ የሚሆነውን ወጪ በመደጎም ለሆስፒታሎች ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝም አስታውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቶራሲክ ሶሳይቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ራሄል አርጋው በበኩላቸው ፤የዓለም የሳንባ ካንሰር ቀን ህብረተሰቡ ስለ ሳንባ ካንሰር ያለውን ግንዛቤ ለማሳደግ እና በበሽታው ላይ የሚደረግ ምርምርን ለመደገፍ ያለመ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡
የሳንባ ካንሰር ተጋላጭነትን በመፈተሽ የቅድመ ልየታ እና ክትትል ስራ አዲስ አበባን ጨምሮ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ እና በአፋር ክልሎች በተመረጡ የጤና ተቋማት መጀመሩን አስታውሰዋል፡፡
በሳንባ ካንሰር ላይ የሚደረጉ የምርምር እና ጥናት ውጤቶች ውስንነት ስለሚታይባቸው የኢትዮጵያ ቶራሲክ ሶሳይቲ በዘርፉ ላይ መስራት ከሚፈልጉ ባለድርሻ አካላት ጋር ተባብሮ ለመስራት ጥልቅ ፍላጎት እንዳለው አብራርተዋል፡፡
ሲጋራና ሺሻ ማጨስ፣ ለከባድ ጭስ መጋለጥ፣ በስራ ቦታ ለመርዛማ ብናኞች መጋለጥ እና ስር የሰደደ የመተንፈሻ አካል ችግር ለበሽታው አጋላጭ መሆናቸው በባለሙያዎቹ ተገልጿል፡፡
የግል ጥንቃቄና የባህርይ ለውጥ ማምጣት እንዲሁም የህክምና ክትትል ማድረግና በሽታውን ለመከላከልና ለመግታት ጉልህ ሚና አላቸው ፡፡