የባህርዳር ስታዲየም አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ውድድሮችን ማስተናገድ እንዲችል ተደርጎ እየተገነባ ነው - አቶ ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
የባህርዳር ስታዲየም አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ውድድሮችን ማስተናገድ እንዲችል ተደርጎ እየተገነባ ነው - አቶ ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 25/2016(ኢዜአ)፡- የባህርዳር ስታዲየም አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ውድድሮችን ማስተናገድ እንዲችል ተደርጎ እየተገነባ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የግንባታ ሂደትን ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ የኢፌዴሪ የጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰ፣ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል ዘላለም መንግሥቴ እና የአማራ ክልል አመራሮች ተገኝተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጉብኝቱ በኋላ የባህር ዳር ስታዲየም አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ውድድሮችን ማስተናገድ እንዲችል ተደርጎ እየተገነባ መሆኑን ገልጸዋል።
በቀጣይ አመት ግንባታው ተጠናቆ ጨዋታዎችን ማስተናገድ እንዲችል ለማድረግም ድጋፎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
ከ12 ዓመት በፊት የተጀመረው የስታዲየሙ ግንባታ በተለያዩ ምክንያቶች ተጓትቶ መቆየቱ ይታወሳል።
መንግሥት ችግሩን ለመቅረፍ ከ2015 ታህሳስ ጀምሮ 1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በመመደብ እንደአዲስ ግንባታውን አስጀምሯል።
በዚህም የካፍን የመመዘኛ መስፈርት ያሟሉ የስፖርት መሰረተ ልማቶች እየተገነቡለት ሲሆን በአሁኑ ወቅት አጠቃላይ ግንባታው 57 በመቶ መድረሱ ተገልጿል።
ግንባታውን በ2017 ዓመተ ምህረት አጋማሽ ለመጨረስ በተለያዩ የግንባታ ዘርፎች 47 የሀገር ውስጥና የውጭ ተቋራጮች እየተሳተፉ መሆኑ ተገልጿል።
በግንባታው የፊፋና የካፍ ደረጃን ያሟላ የመጫወቻ ሜዳና የሳር ዝግጅት ስራ፣ የትኬት ቢሮ፣ የመግቢያ በሮች፣ የመልበሻ ክፍሎች፣ በማታ ማጫወት የሚያስችሉ መብራቶች፣ የተመልካችና የልዩ እንግዶች መቀመጫዎችን ጨምሮ የተለያዩ መሠረተ ልማቶች እየተገነቡ መሆኑም እንዲሁ።
ከጉብኝቱ በኋላም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩና ሌሎች አመራሮች በስታዲየሙ ዙሪያ የአረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።