ቀጥታ፡

የኃይማኖት ተቋማት ሰላምን ለማረጋገጥ እያደረጉ ያለውን አስተዋጽኦ አጠናክረው መቀጠል አለባቸው 

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 25/2016(ኢዜአ)፦ የኃይማኖት ተቋማት በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ እያደረጉ ያለውን አስተዋጽኦ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ጥሪ አቀረቡ። 

የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባዔ 16ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔና የዕውቅና መድረክ "በጎ ለዋሉልን እናመስግን፤  ሰላማችንን እንጠብቅ" በሚል መሪ ኃሳብ እያካሄደ ነው።  

በመርኃ-ግብሩ ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ፣ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር)፣ የኃይማኖት ተቋማት መሪዎችና የተለያዩ እንግዶች ተገኝተዋል። 

ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ የኃይማኖት መሪዎች በምዕመናን ያላቸውን ተሰሚነት ተጠቅመው ለዘላቂ ሰላም መስፈን መሥራት አለባቸው። 

ሰላም ከሌለ ልማትና እድገትን ማረጋገጥ እንደማይቻል ጠቅሰው፤  ሰላምን ለማፅናት የተባበረ ክንድ እንዲሁም  የኃይማኖት አስተምህሮ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።   

በመሆኑም የኃይማኖት ተቋማት በሀገሪቱ ሰላምን ለማረጋገጥ እያከናወኑ ያለውን ተግባር አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል። 

የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ከይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የኃይማኖት ተቋማት ሀገርን በዘመናት ለማስቀጠል ሚናቸውን ሲወጡ መቆየታቸውን ተናግረዋል። 

ሚኒስቴሩ በሰላምና አብሮነት ዙሪያ ከኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ጋር እያከናወነ ያለውን ሥራ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል። 

የጉባዔው የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ሰብሳቢ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ፤ ጉባዔው በሰላምና መከባበር እሴት ግንባታ ላይ በትብብር ለመሥራት የተመሠረተ መንፈሳዊ ተቋም ነው ብለዋል። 

ይህንንም ተከትሎ በአገሪቱ ሕዝቦችና የኃይማኖት ተቋማት መካከል ለዘመናት የዘለቀውን የመከባበርና የመደጋገፍ ባህልን ለማጠናከርና ለትውልድ ለማስተላለፍ ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል። 

የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ለሰላም፣ መከባበርና አብሮነት እሴቶችን ማጎልበት የጀመረውን ጥረት ይበልጥ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ አረጋግጠዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም