ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የግንባታ ሂደትን ጎበኙ - ኢዜአ አማርኛ
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የግንባታ ሂደትን ጎበኙ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 25/2016(ኢዜአ)፦ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የግንባታ ሂደትን ጎበኙ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባህርዳር ኤርፖርት ሲደርሱ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋ።
ከዚህ በኋላ በነበረው ጉብኝትም የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጀኔራል አበባው ታደሰ፣ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ ኃላፊ ምክትል ኮማሽነር ጀነራል ዘላለም መንግሥቴ፣ የክልሉ አመራሮች ተገኝተዋል።
ከጉብኝቱ በተጓዳኝም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩና ሌሎች አመራሮች በስታዲየሙ ዙሪያ አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።
ከ12 ዓመት በፊት የተጀመረው የስታዲየሙ ግንባታ በተለያዩ ምክንያቶች ተጓቶ መቆየቱ ይታወሳል።
መንግሥት ችግሩን ለመቅረፍ ከ2015 ዓም ታህሳስ ጀምሮ 1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በመመደብ እንደ አዲስ ግንባታውን አስጀምሯል።
በዚህም የካፍን የመመዘኛ መስፈርት ያሟሉ የስፖርት መሰረተ ልማቶች እየተገነቡለት ሲሆን በአሁኑ ወቅት አጠቃላይ ግንባታው ደግሞ 57 በመቶ መድረሱ ተገልጿል።
ግንባታውን በ2017 ዓም አጋማሽ ለመጨረስ በተለያዩ የግንባታ ዘርፎች 47 የሀገር ውስጥና የውጭ ተቋራጮች እየተሳተፉ ነው ተብሏል።
በግንባታው የፊፋና የካፍ ደረጃን ያሟላ የመጫወቻ ሜዳና የሳር ዝግጅት ስራ፣ የትኬት ቢሮ፣ የመግቢያ በሮች፣ የመልበሻ ክፍሎች፣ በማታ ማጫወት የሚያስችሉ መብራቶች፣ የተመልካችና የልዩ እንግዶች መቀመጫዎችን ጨምሮ የተለያዩ መሠረተልማቶች እየተገነቡ መሆኑም እንዲሁ።