የኢትዮጵያና ቻይና የንግድና ኢንቨስትመንት አጋርነት ለማጠናከር የሚሰሩ ሥራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያና ቻይና የንግድና ኢንቨስትመንት አጋርነት ለማጠናከር የሚሰሩ ሥራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 24/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያና ቻይና መካከል ያለውን የንግድና ኢንቨስትመንት አጋርነት ለማጠናከር የሚሰሩ ሥራዎች ተጨባጭ ውጤት እያመጡ መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ገለጸ።
የኢትዮ-ቻይና የወዳጅነት ትብብር ኮሚቴ ያዘጋጀው ሁለተኛው የኢትዮ-ቻይና ወዳጅነት ትብብር መድረክ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
የኢትዮጵያን የኢንዱስትሪ ሴክተር መጠናከር የሚያግዝ የመግባቢያ ሥምምነት በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንና በኢትዮ-ቻይና የወዳጅነት ትብብር ኮሚቴ መካከል ተፈርሟል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሃና አርአያሥላሴ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት በውጭ ባለሃብቶች ዘንድ ተመራጭነቷ እያደገ መጥቷል።
ይህንንም ተከትሎ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እያደገ መሆኑን ገልጸው ለዚህም ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢ መኖሩና በፈተናዎች ሁሉ የሚያልፍ ጠንካራና ፈጣን ኢኮኖሚ እድገት መስመዝገብ መቻሏን በምክንያት አስቀምጠዋል።
የቻይና ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች የሚያደርጉት ተሳትፎ እየጨመረ መምጣቱን ገልጸው የኢትዮ-ቻይና ወዳጅነትና ትብብር ኮሚቴም የሁለቱ አገራት የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስር ይበልጥ እንዲሳለጥ እያገዘ መሆኑን ጠቁመዋል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ለኢነርጂ ልማት የተመቸ ነባራዊ ሁኔታ እንዳላት ገልጸው በተለይም ኢትዮጵያ ርካሽ የኤሌክትሪክ ታሪፍ ካላቸው አገራት ግንባር ቀደሟ መሆኗን ተናግረዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በመድረኩ በተወካያቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ ኢትዮጵያ የቤልትና ሮድ ኢንሼቲቭን በመቀበል ግንባር ቀደም መሆኗን ገልጸዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከኢትዮ-ቻይና ወዳጅነትና ትብብር ኮሚቴ ጋር በጋራ ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን ገልጸው በኢትዮጵያና ቻይና መካከል ያለውን አጋርነት ለማሳደግ ሚኒስቴሩ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።
የኢትዮ-ቻይና ወዳጅነትና ትብብር ኮሚቴ ሊቀ-መንበር ቤቲ ሱ ዛሬ የተፈረመው የመግባቢያ ሥምምነት ለኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ሴክተር አድገት አዎንታዊ አበርክቶ አለው ብለዋል።