ቀጥታ፡

ቤተ ክርስቲያኗ በመሬት መንሸራተት አደጋ ምክንያት ቤተሰቦቻቸውን ላጡና ለተፈናቀሉ ወገኖች የ11 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገች

ሳውላ፤ ሐምሌ 24/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ በደረሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ ምክንያት ቤተሰቦቻቸውን ላጡና ለተፈናቀሉ ወገኖች የ11 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገች።

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተወከሉ ብፁዓን ድጋፉን ለጎፉ ዞን አስተዳደር አስረክበዋል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን የስብክተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ማርቆስ በአደጋው ለተጎዱ ወገኖች የገንዘብ ድጋፉን እና የእምነቱ ተከታዮች ከሆኑ የአንድ ቤተሰብ አባላት የተበረከተውን 30 ኩንታል ዱቄት ድጋፍም አስረክበዋል።

የደቡብ ኦሞና አሪ ዞኖች ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ብፁዕ አቡነ ፊሊጶስ ከሀጉረ ስብከቶቹ የተበረከተ 100 ኩንታል ዱቄትም በድጋፍ አስረክበዋል።

የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ዳግማዊ አየለ የሃይማኖት ተቋማቱ ላደረጉት ድጋፍ በዞኑ አስተዳደርና በተጎጂዎች ስም አመስግነዋል።

ተጎጂዎችን ለመደገፍና በዘላቂነት ለማቋቋም የሚረዱ ተግባራት በቅንጅት በመከናወን ላይ እንደሚገኙም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም