የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የብድር ጫናን ትርጉም ባለው መልኩ በመቀነስ የተረጋጋ የኢኮኖሚ ምህዳር የሚፈጥር ነው - አቶ አሕመድ ሽዴ - ኢዜአ አማርኛ
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የብድር ጫናን ትርጉም ባለው መልኩ በመቀነስ የተረጋጋ የኢኮኖሚ ምህዳር የሚፈጥር ነው - አቶ አሕመድ ሽዴ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 24/2016(ኢዜአ)፦ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የብድር ጫናን ትርጉም ባለው መልኩ በመቀነስ የተረጋጋና ህዝብን ተጠቃሚ የሚያደርግ የኢኮኖሚ ምህዳር እንደሚፈጥር የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ ተናገሩ፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአስቸኳይ ስብሰባው ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ የልማት ማኅበር ጋር ያደረገችውን የፋይናንስ ድጋፍ ሥምምነት በአብላጫ ድምጽ አፀድቋል።
የዓለም አቀፉ የልማት ማኅበር ለመጀመሪያው ዘላቂና ሁሉን አቀፍ የእድገት ልማት ፖሊሲ ማስፈጸሚያ የሚውል 1 ቢሊየን ዶላር እርዳታ እንዲሁም 500 ሚሊየን ዶላር ብድር በድምሩ 1 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር እርዳታና ብድር ለኢትዮጵያ መንግሥት ለመስጠት መስማማቱን ተከትሎ ከማኅበሩ ጋር የገንዘብ ድጋፍና የብድር ሥምምነት መፈረሙን ጠቅሰዋል።
በብድር የተገኘው ገንዘብ ሙሉ በሙሉ በአንድ ጊዜ ወደ መንግሥት ትሬዥሪ የሚፈስ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግሥት የጀመራቸውን የሪፎርም ሥራዎች ለማገዝ እንዲሁም የፌዴራል መንግሥትን የ2017 በጀት በቀጥታ ለመደገፍ የሚውል መሆኑንም ተገልጿል፡፡
የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ ስምምነቱን አስመልክቶ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በማብራሪያቸውም አገራዊ ለውጡን ተከትሎ መንግስት የኢኮኖሚ ስብራትን ለማስተካከል የመጀመሪያው ሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ በማዘጋጀት ወደ ስራ መግባቱን አንስተዋል፡፡
በመጀመሪያው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ በርካታ ውጤት ማስመዝገብ ቢቻልም ዓለም አቀፍና የሀገር ውስጥ ጫና በመኖሩ በሚፈለገው ልክ ዕድገትን ማስቀጠል አንዳልተቻለ አንስተዋል።
ባለፉት ስድስት ዓመታት ኢትዮጵያ ምንም አይነት የንግድ ብድር አለመውሰዷን ጠቅሰው፤ በአንጻሩ ያለብንን የብድር ጫና ለመቀነስ የሚያስችሉ በርካታ ስራዎች ተከናውነዋል ነው ያሉት፡፡
ከዓለም አቀፉ የልማት ማኅበር የተገኘው ብድርም በረዥም ጊዜ የሚከፈል ቀላል ብድር መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ወደ ተሟላ ትግበራ የገባው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያም የኢትዮጵያን የእዳ ጫና ለማቃለል በሚከናወኑ ስራዎች ውስጥ ትርጉም ያለው ለውጥ እንደሚያመጣም ተናግረዋል፡፡
ለአብነትም ከዓለም አቀፉ ገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) ከሚገኘው 10 ነጥብ 5 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር ውስጥ 3 ነጥብ 5 ቢሊየን የሚሆነው የዕዳ ቅነሳን ለማከናውን የሚደረጉ ስራዎችን የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል።
ማሻሻያው እድገትን በዘላቂነት ለማስቀጠል፣ የግሉ ሴክተርን በኢኮኖሚው ውስጥ በስፋት ለማሳተፍ እንዲሁም የኢንቨስትመንት ፍሰትን ለማሻሻል ሚናው የጎላ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ይህም የማክሮ ኢኮኖሚውን በማረጋጋት በተጨባጭ ህዝብን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ነው የተናገሩት፡፡
የማክሮ ኢኮኖሚው መረጋጋት ደግሞ የዋጋ ንረትን በዘላቂነት ለመቋቋም ብቸኛው መፍትሄ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ማሻሻያው በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ ዜጎችን ለመደገፍም ከደሞዝ ባሻገር፣ የነዳጅ፣ ዘይት፣ የማዳበሪያና የመድሃኒት ግዥ ድጎማ እንደሚያደርግ አውስተዋል፡፡
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ሂደት ተከትሎ በኢኮኖሚው ውስጥ ሊከሠት የሚችለውን የመልካም አስተዳደር ብልሹነት እና ሕገ ወጥነት ለመከላከል መንግሥት በከፍተኛ ጥንቃቄ ቁጥጥር በማድረግ እርምጃ እንደሚወስድም ጠቁመዋል፡፡