ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የውኃ አዘል ኃብቶቿን ተጠቅማ የኢኮኖሚ እድገቷን ለማሳለጥ የምታከናውነው ተግባር የሚበረታታ ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 24/2016(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ የውኃ አዘል ኃብቶቿን በማልማትና በመጠቀም የኢኮኖሚ እድገቷን ለማሳለጥ የምታከናውነው ተግባር የሚበረታታ መሆኑን የአፍሪካ ኅብረት ገለጸ።

ኢትዮጵያ የውኃ አዘል ኃብቶቿን በማልማት ምጣኔ ኃብታዊ ተጠቃሚነቷን ለማሳደግ ከዓመት በፊት የብሉ ኢኮኖሚ (የባህር፣ የጠረፍና የውኃ ኃብቶች አጠቃቀም) የአምስት ዓመት ስትራቴጂ ሰነድ አዘጋጅታ ወደ ሥራ አስገብታለች። 

ስትራቴጂው ኢትዮጵያ የባህር በር ባይኖራትም ሐይቆቿን፣ ወንዞቿን፣ የከርሰ-ምድር ውኃና ተዛማጅ የውኃ ኃብቶችን ለማልማትና ለመጠቀም ትኩረት ታደርጋለች ተብሏል። 

ስትራቴጂው የኢትዮጵያን የምርት ብዝኃነቷን ለማስፋት እንደሚረዳም ተመላክቷል።    

የአፍሪካ ኅብረት የዘላቂ ከባቢ አየርና ብሉ ኢኮኖሚ ዳይሬክቶሬት የብሉ ኢኮኖሚ ዘርፍ ኃላፊ ጆርጅ ምባ አሴኮ፤ አፍሪካ በብሉ ኢኮኖሚ የኢኮኖሚ እድገቷን ማሳለጥ የምትችልበት አቅም አላት ብለዋል።

ለዚህም አፍሪካ 47 በመቶ የቆዳ ስፋቷ በሐይቆች፣ በወንዞችና በሌሎች አካላት መሸፈኑንና በሕንድ ውቅያኖስ፣ በአትላንቲክ ውቅያኖስ፣ በሜዲትራንያን ባህርና ቀይ ባህር የተከበበች መሆኗንም አንስተዋል። 

ይህንንም ተከትሎ የአፍሪካ ኅብረት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2020 አንስቶ የብሉ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ እየተገበረ መሆኑን ገልፀዋል።

ብሉ ኢኮኖሚ የባህር በር የሌላቸው አገራትንም ጭምር አቅፎ የያዘ በመሆኑ ኢትዮጵያ ባሏት በርካታ የውኃ ኃብቶች የዘርፉ ተጠቃሚ መሆን እንደምትችል ተናግረዋል።

ኢትዮጵያም ይህንኑ ከግምት ውስጥ በማስገባት የብሉ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ ቀርፃ ወደ ትግበራ መግባቷን ጠቅሰው፤ በውኃና ውኃ አዘል ኃብቶቿ በዓሳ ምርት፣ ቱሪዝም፣ ትራንስፖርት፣ ኢነርጂና ሌሎች መስኮች ያሉ የኢኮኖሚ ዕድሎች ይዛለች ብለዋል።

ኢትዮጵያ በብሉ ኢኮኖሚ ዘርፍ በጥሩ ጎዳና ላይ ትገኛለች ያሉት ኃላፊው፤ አገሪቷ በዘርፉ ለማደግ ከፍተኛ አቅም እንዳላት ገልጸው፤ የአፍሪካ ኅብረት ኢትዮጵያ በብሉ ኢኮኖሚ ለምታከናውናቸው ሥራዎች ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልፀዋል።


 

በተያያዘም የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ-መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) የአካባቢ ጥበቃ ፕሮግራም  ማናጀር እሸቴ ደጀን (ዶ/ር)፤ ኢጋድ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2021 አንስቶ ቀጣናዊ የብሉ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ እየተገበረ ይገኛል ብለዋል።

ስትራቴጂው ከአፍሪካ ኅብረት የዘርፉ ስትራቴጂ ጋር የተጣጣመ መሆኑን ገልፀዋል። 

ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች አባል አገራት በስትራቴጂው አማካኝነት የራሳቸውን ብሔራዊ ስትራቴጂ በማዘጋጀት እየተገበሩ ይገኛል ብለዋል። 

ኢጋድ ለኢትዮጵያ የብሉ ኢኮኖሚ ስትራቴጂው ቀረፃ የቴክኒክ ድጋፍን ማድረግ ጨምሮ ወደ ትግበራ ከገባ በኋላም ለአፈጻጸሙ የሚያስፈልገውን ኃብት ማፈላለግና የአቅም ግንባታ ድጋፎችን ማድረጉን አመልክተዋል።

ኢጋድ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ጋር በመሆን ኢትዮጵያ በብሉ ኢኮኖሚ ያላትን ኃብትና በዘርፉ ልታገኝ የምትችለውን የማኅበራዊና ኢኮኖሚ ጠቀሜታዎች አስመልክቶ ያደረገውን ሁሉን አቀፍ ጥናት በቅርቡ ይፋ እንደሚያደርግም ጠቁመዋል።

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ብሉ ኢኮኖሚ ስትራቴጂን ከሌሎች ተቋማት ጋር በመሆን በጋራ የሚያስፈጽም ሲሆን፤ ኢጋድ የኢትዮጵያን የብሉ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ የድርጊት መርኃ-ግብር በቅርቡ ማጽደቁ ይታወሳል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም