ቀጥታ፡

በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፍ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተሻለ አፈጻጸም የተመዘገበባቸው ተግባራት ተከናውነዋል

ሆሳዕና ፤ ሐምሌ 24/2016 (ኢዜአ)፦በትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ዘርፍ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተሻለ አፈጻጸም የተመዘገበባቸው ተግባራት መከናወናቸውን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸምን በሆሳዕና ከተማ እየገመገመ ሲሆን በበጀት ዓመቱ በዘርፉ በተሰሩ ሥራዎች ከ3 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ለማዳን መቻሉም ተገልጿል።


 

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ደንጌ ቦሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በዘርፉ የተሻለ አፈጻጸም የተመዘገበባቸው ተግባራት ተከናውነዋል። 

ሀገራዊ የልማት ግቦችን ለማሳካት ፤ሃገሪቱ ተጀመረችውን ጉዞ ለማፈጠን ዘርፉ የሚኖረውን ሚና ለማጠናከር የተለያዩ ሥራዎች መከናወናቸውንም አንስተዋል። 

በበጀት ዓመቱ በዘርፉ ይስተዋሉ የነበሩ ብልሹ አሰራሮችን በማረም ለዜጎች ፍትሃዊ አገልግሎትን ተደራሽ በማድረግ ውጤታማ ሥራዎች መሰራታቸውንም ነው የገለጹት።

የትራንስፖርት አገልግሎት በሚሰጡ ተቋማት ላይ የሚስተዋሉ የስነ ምግባር ጥሰቶችን ለማረም እንዲቻል በተቀናጀ መልኩ በተሰራ ሥራም ውጤት መገኘቱን አቶ ደንጌ ተናግረዋል።

ለአብነትም የታሪፍና ተያያዥ ችግሮችን ለመፍታት የሚረዳ ዘመናዊ የክፍያ ስርዓት በመዘርጋት በህገወጥ መንገድ ሲደረግ የነበረን የታሪፍ ጭማሪን ማስቀረት መቻሉን ጠቁመው፣ በቀጣይም ይህን ለማስፋት ይሰራል ብለዋል።

የታዳሽ ኃይል አማራጭን በመጠቀም በትራንስፖርት ዘርፍ ሲስተዋል የነበረን የአቅርቦት ችግር ለመፍታት ሲሰራ መቆየቱን አቶ ደንጌ ገልጸው፣ በዚህም የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ተደራሽ ለማድረግ ስራዎች መሰራታቸውንና አበረታች ውጤቶች መገኘታቸውን ገልጸዋል።

በሎጂስቲክስ ዘርፍም የሀገሪቱ የወጪና ገቢ ምርቶች አገልግሎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ጠቁመው፣ በበጀት ዓመቱ ማዳበሪያን በማጓጓዝ ወደ ሀገር ወስጥ ማስገባት መቻሉን በማሳያነት አንስተዋል።

መልቲ ሞዳል የትራንስፖርት አገልግሎትን ለማሳደግ በተሰራው ሥራም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ያለአግባብ ይወጣ የነበረ 3 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዶላር ለማዳን ተችሏል ብለዋል። 


 

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመሰረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የመንገድ ልማትና ትራንፖርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር መሀመድ ኑርዬ በበኩላቸው በበጀት ዓመቱ በክልሉ በትራንስፖርት ዘርፍ ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ፣ ትርፍ መጫንና መሰል ችግሮች እንደተስተዋሉ አስታውሰዋል።

ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ የነበሩ ችግሮችን ለመፍታት ከትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ማህበራት ጋር ተነጋግሮ በቅንጅት በመሰራቱ ውጤት መገኘቱን አንስተዋል።  

በተለይም የትራንስፖርት አገልግሎት የህዝብን ፍላጎት መሰረት ባደረገ መልኩ እንዲመራ የተስተዋሉ ውስንነቶችን የመፍታት ስራ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ሚኒስቴሩ በሆሳዕና ከተማ እያካሄደ ባለው መድረክ የሁሉም ክልሎች የዘርፉ አካላት ዕቅድ አፈጻጸም ቀርቦ ውይይት የሚደረግበት ሲሆን የተሻለ አፈጻጸም ያላቸው ክልሎች ተሞክሯቸውን እንደሚያጋርም ታውቋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም