ቀጥታ፡

የናፍቆት ድሬዳዋ በዓል በተለያዩ የኢንቨስትመንት የሚሰማሩ ተወላጆቿ እና ወዳጆቿ እንዲጨምሩ አስችሏል- ከንቲባ ከድር ጁሃር

ድሬዳዋ ፤ሐምሌ 24/2016 (ኢዜአ)፡-የናፍቆት ድሬዳዋ ሳምንት ዓመታዊ በዓል መካሄድ ከጀመረ ወዲህ  በተለያዩ ኢንቨስትመንት ላይ  የሚሰማሩ ተወላጆቿ እና ወዳጆቿ እንዲጨምሩ ማስቻሉን የድሬዳዋ አስተዳድር ከንቲባ ከድር ጁሃር አስታወቁ። 

የናፍቆት ድሬዳዋ  ሳምንት ዓመታዊ በዓል ዛሬ "ድሬ ለኢትዮጵያ ከፍታ" በሚል መሪ ሐሳብ በሲምፖዚየም ተከበሯል።

በሲምፖዚየሙ ላይ የድሬዳዋን የፍቅር፣ የአንድነት እና የሰላም ከተማነት እና አገራዊ ለውጡን ተከትሎ ድሬዳዋ የምስራቅ የአገራችን ክፍል የኢንዱስትሪ እና የንግድ መናኸሪያነት ለማረጋገጥ እየተከናወኑ የሚገኙ ስራዎች እና ምቹ ሁኔታዎችን የተመለከተ ጥናታዊ ፅሁፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

ጥናታዊ ፅሑፉ በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ክፍል ዲን ሮባ ጴጥሮስ(ዶ/ር) የቀረበ ሲሆን፤ ውይይቱን የመሩት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚደንት ዑባህ አደም(ዶ/ር) ናቸው።

በሲምፖዚየሙ ላይ የተገኙት ከንቲባ ከድር ጁሃር እንዳሉት፤ አገራዊ ለውጡን ተከትሎ በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ማህበረሰብ አባላት የድሬዳዋ እና የአገርን ከፍታ ለማረጋገጥ በሚከናወኑ ተግባራት ላይ ወሳኝ ሚና እየተጫወቱ ናቸው።

በተለይም የናፍቆት ድሬዳዋ ሳምንት ዓመታዊ በዓል መካሄድ ከጀመረ ወዲህ  በተለያዩ የኢንቨስትመንት ስራዎች ላይ የሚሰማሩ ተወላጆቿ እና ወዳጆቿ እየጨመሩ ነው ብለዋል።

እነዚህ ተግባራት  ለዜጎች የስራ ዕድል በመፍጠርና ተኪ ምርቶችን በማምረት የውጭ ምንዛሬን እያስገኙ መሆናቸውን በማንሳት።

የድሬዳዋንና የምስራቁን የኢትዮጵያ ህዝብ የኩላሊት ዕጥበት ህክምና ችግር በመፍታት እና የህክምና መገልገያዎች ችግሮች በማሟላት በጤናው ዘርፍ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዲጎለብት ያከናወኗቸው ስራዎችን ለአብነት አንስተዋል።

ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ማህበረሰብ የድሬዳዋ እና የአገርን ከፍታ ለማሳደግ የሚያከናውኑትን ስራዎች ለማሳደግ አስተዳደሩ የሚያደርገውን ድጋፍ እና ዕገዛ አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።

በመላው ዓለም የሚገኙት ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ማህበረሰብ አባላት የጀመሯቸውን አበረታች ተግባራት አጠናክረው እንዲቀጥሉ በመጠየቅ።

በሲምፖዚየሙ ላይ በመሳተፍ ላይ ያሉት እንግዶች በበኩላቸው መንግስት በውጭ አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የዳያስፖራው የማህበረሰብ አባላት በአገር ሰላም እና ልማት ላይ እንዲሳተፍ እያደረገ የሚገኘው ድጋፍ የሚበረታታ መሆኑን ገልፀዋል።

በአሜሪካ የሚኖሩት ትውልደ ኢትዮጵያዊ አቶ ሲሳይ በቀለ በሰጡት አስተያየት የድሬዳዋ አስተዳደርም ሆነ የፌዴራል መንግስት ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ያላቸውን ሃብት፣ ዕውቀት እና ቴክኖሎጂ በአገራቸው ልማት ላይ እንዲያውሉ የሚያደርጉት ጥረት የሚበረታታና ሁሉንም የሚጋብዝ ነው ብለዋል።

"ይህንን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም በ420 ሚሊዮን ብር የህክምና ግብዓት ማምረቻ ፋብሪካ ገንብቼ ወደ ስራ ገብቻለሁ" ብለዋል።

"እንደ ድሬደዋ ተወላጅነቴ የድሬዳዋን ማህበራዊ ችግሮች ለመፍታት እና በበጎ ተግባራት ላይ የድርሻዬን ለመወጣት ተዘጋጅቻለሁ" ያሉት  ደግሞ ከዩናይትድ አረብ ኤምሬት  የመጡት ወይዘሮ  ሐረገወይን ሙሉጌታ ናቸው።

ናፍቆት ድሬዳዋ ሳምንት ከድሬ እና ከአገራችን ጋር ያለንን ትስስር ይበልጥ ለማጠናከርና በአገር ልማት ላይ የድርሻችንን እንድንወጣ አድርጎናልም ብለዋል።

ዛሬ ለአንድ ቀን በተካሄደው ሲምፖዚየም ላይ የድሬዳዋ ልማት ማህበር  ህዝቡንና በውጭ አገራት የሚገኙ የድሬዳዋ ተወላጆች እና ወዳጆችን በማስተባበር የአስተዳደሩ ማህበራዊ ችግሮች ለመፍታት እያከናወናቸው የሚገኙትን መሠረታዊ ስራዎች አስረድቷል።

በሲምፖዚየሙ ላይ  የድሬዳዋ አስተዳደር የካቢኔ አባላት፣ የኃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች እና በየደረጃው የሚገኙ የህብረተሰብ ተወካዮች ተሳታፊ ሆነዋል።

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም