የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በገዜ ጎፋ ወረዳ በመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በገዜ ጎፋ ወረዳ በመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ አደረገ
ሶዶ፤ሐምሌ 24/2016 (ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በገዜ ጎፋ ወረዳ በቅርቡ በተከሰተው የመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የምግብና የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ ሀጂ ኢብራሂም ቱፋ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ምክር ቤቱ በወረዳው በደረሰ የመሬት መንሸራተት አደጋ ሳቢያ በሰዎች ላይ በደረሰ ጉዳት ጥልቅ ሀዘን ተሰምቶታል።
አደጋው ከተሰከተ ጀምሮ ምክር ቤቱ ተጎጂዎችን ለማጽናናትና ድጋፍ ለማድረግ ሲሰራ መቆየቱን አውስተዋል።
በዛሬው ዕለትም 200 ኩንታል የዳቦ ዱቄት፣ 3 ሺህ ቆርቆሮ፣ ሚስማር እና የተለያዩ ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸው፣ ድጋፉ ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚገመት ተናግረዋል።
በአደጋው የተጎዱ ዜጎችን ለማቋቋም የሚከናወኑ ሥራዎችን ለማገዝ ምክር ቤቱ በቀጣይም የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
ድጋፉን የተረከቡት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አማካሪና ተወካይ ዶክተር ብርሃኑ ጌቦ በበኩላቸው፣ በወረዳው ኬንቾ ሻቻ ጎዝዲ ቀበሌ በደረሰ የመሬት መንሸራተት አደጋ ሳቢያ በወገኖች ላይ ልብ ሰባሪ ጉዳት መድረሱን አስታውሰዋል።
በአደጋው ቤተሰቦቻቸውን ያጡና ተጎጂዎችን ለማቋቋም በተቀናጀ መልኩ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው፣ ምክር ቤቱ ዛሬ ያደረገው ድጋፍ ይህን እንደሚያግዝ ገልጸው ምስጋና አቅርበዋል።
በወረዳው በቅርቡ የተከሰተው የመሬት መንሸራተት አደጋ ለበርካታ ዜጎች ህይወት መጥፋትና ንብረት መውደም ምክንያት መሆኑም ይታወሳል።