የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ የልማት ማኅበር ጋር ያደረገችውን የፋይናንስ ድጋፍ ሥምምነት አፀደቀ - ኢዜአ አማርኛ
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ የልማት ማኅበር ጋር ያደረገችውን የፋይናንስ ድጋፍ ሥምምነት አፀደቀ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 24/2016(ኢዜአ)፦ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአስቸኳይ ስብሰባው ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ የልማት ማኅበር ጋር ያደረገችውን የፋይናንስ ድጋፍ ሥምምነት በአብላጫ ድምጽ አፀደቀ።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 38ኛ መደበኛ ስብሰባው ዓለም አቀፍ የልማት ማኅበር ጋር የተደረገውን የፋይናንስ ድጋፍ ሥምምነት ለማፅደቅ በተዘጋጀው አዋጅ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።
ከዓለም አቀፍ የልማት ማኅበር ጋር የተደረገው የፋይናንስ ድጋፍ ሥምምነት የ1 ነጥብ 5 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር የሚያስገኝ ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ 1 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር በእርዳታ፣ 500 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ደግሞ በብድር መልክ የተገኘ ነው።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሰነዱ ላይ ከተወያየ በኋላ ከአገሪቱ የብድር አስተዳደር ስትራቴጂ ጋር የሚጣጣም መሆኑን በማረጋገጥ ሥምምነቱን አፅድቆ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምፅ ወስኗል።
ይህንንም ተከትሎ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአስቸኳይ ስብሰባው ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ የልማት ማኅበር ጋር ያደረገችውን የፋይናንስ ድጋፍ ሥምምነት ላይ ተወያይቷል። በምክር ቤቱ የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) የብድር ሥምምነት ረቂቅ አዋጁን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ፤ ከለውጡ በኋላ ገቢራዊ የሆነው የመጀመሪያው አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ብዙ ውስጣዊና ውጫዊ ፈተናዎችን ተቋቁሞ መልካም ውጤት አስመዝግቧል ብለዋል።
ባለፉት የለውጥ ዓመታትም በአማካይ 6 ነጥብ 2 በመቶ እድገት ማስመዝገብ የተቻለበት መሆኑን ጠቅሰዋል።
በሁለተኛው የአገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም እንቅስቃሴ፤ የማክሮ ስብራቶችን ለመጠገን እንዲሁም በመጀመሪያው ምዕራፍ የተገኘውን ውጤት ለማስቀጠል በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በዚህ መሠረት፤ የማክሮ ኢኮኖሚውን ለማረጋጋት በተለይም ለሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የዋጋ ግሽበትን ለመቀነስ ለመቆጣጠር፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ለመቅረፍና የመዋቅር ማስተካከያ ለማምጣት የሚያስችሉ የሪፎርም ሥራዎች ወደ ሥራ ገብተዋል ብለዋል።
ለዓለም አቀፉ የልማት ማኅበር ይህንን የተሟላ የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ-ግብር ለመደገፍ በቀጥታ ለበጀት ድጋፍ ለማድረግ ለመጀመሪያው ዘላቂና ሁሉን አቀፍ የእድገት ልማት ፖሊሲ ማስፈጸሚያ የሚውል 1 ቢሊየን ዶላር እርዳታ እንዲሁም 500 ሚሊየን ዶላር ብድር በድምሩ 1 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር እርዳታና ብድር ለኢትዮጵያ መንግሥት ለመስጠት መስማማቱን ተከትሎ ከማኅበሩ ጋር የገንዘብ ድጋፍና የብድር ሥምምነት መፈረሙን ጠቅሰዋል።
በብድር የተገኘው ገንዘብ ሙሉ በሙሉ በአንድ ጊዜ ወደ መንግሥት ትሬዥሪ የሚፈስ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግሥት የጀመራቸውን የሪፎርም ሥራዎች ለማገዝ እንዲሁም የፌዴራል መንግሥትን የ2017 በጀት በቀጥታ ለመደገፍ የሚውል መሆኑን ጠቅሰዋል።
በተለይም 500 ሚሊየን ዶላር ብድሩ ከወለድ ነፃ፤ ባንኩ በሚወስነው መሠረት ጥቅም ላይ ባልዋለው የብድር ገንዘብ ላይ በዓመት እስከ 0 ነጥብ 5 በመቶ የሚደርስ የግዴታ ክፍያ ሊከፈልበት ይችላል ብለዋል።
ባንኩ የብድሩን ገንዘብ በማስተዳደር ረገድ ለሚሰጠው አገልግሎት 0 ነጥብ 75 በመቶ የአገልግሎት ክፍያ እንደሚከፈልበትም አስረድተዋል።
በተጨማሪም ብድሩ የስድስት ዓመት የችሮታ ጊዜን ጨምሮ በ38 ዓመታት ውስጥ ተከፍሎ የሚጠናቀቅ መሆኑን ገልጸው፤ ምክር ቤቱ የድጋፍ ሥምምነቱን እንዲያፀድቅ ጠይቀዋል።
ምክር ቤት በድጋፍ ሥምምነቱ ላይ ከተወያየ በኃላ በአብላጫ ድምፅ አፅድቋል።