ቀጥታ፡

ጥንዶቹ የልብ ሐኪሞች ወገኖቻቸውን ለመርዳት  ወደ አገራቸው  ሊገቡ ነው

አዲስ አበባ፤  ሀምሌ 24/2024 (ኢዜአ)፦ጥንዶቹ የልብ ሐኪሞች ወገኖቻቸውን ለመርዳት  ወደ አገራቸው  ሊገቡ ነው።

ኑሯቸውን በአሜሪካ አትላንታ ያደረጉት ኢትዮጵያውያን ጥንዶች በህክምና ሞያቸው  ወገኖቻቸውን ለመርዳት ወደ ትውልድ ሀገራቸው ኢትዮጵያ እንደሚመጡ በመጪው ወር    እንደሚጓዙ የፎክስ ኒውስ ዘገባ ያመለክታል።

የልብ ሀኪሞቹ  ከአንድ ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚገመት የህክምና ቁሳቁስ ይዘው እንደሚጓዙም በዘገባው ተጠቅሷል ።

ዶክተር ተስፋዬ ተሊላ በፒየድሞንት ኒውናን ሆስፒታል ኢንተርቬንሽናል ካርዲዎሎጂስት ሲሆኑ፤ ባለቤታቸው ዶክተር ኦብሲኔት መርድ ደግሞ በሞርሃውስ የህክምና ትምህርት ቤት የህክምና ትምህርት ባልደረባ ናቸው።

ጥንዶቹ ትምህርታቸውን በሚኖሩበት ከተማ ተምረው እዛው ስራቸውን ቢያደርጉም   ወገኖቻቸውን   ለማርዳት በማለም  “ኸርት አታክ ኢትዮጵያ” የተባለ ግብረ-ሰናይ ድርጅት በመመስረት የልብ ህሙማን ለመርዳት  የበኩላቸውን እየተወጡ ነው።

ጥንዶቹ የህክምና ባለሞያዎች በጉዞአቸው አራት ዶክተሮችንና  አጋዥ ባለሙያዎችን ያቀፈ 16 አባላት  የህክምና ቡድንን ይዘው እንደሚመጡ ዘገባው ሲያትት  የእነሱን መምጣት ከ6 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን የልብ ህሙማን እየተጠባበቁም ናቸው ።

ዶክተር ተስፋዬ “ለአገራቸው ብዙ መስራት የሚችሉ ወጣቶች በጸና ታመው የሌሎችን እገዛ ሲጠብቁ ማየት ኅሊናን የሚረብሽ ነው “ ብለዋል ።

ጥንዶቹ የልብ ሐኪሞች “ኸርት አታክ ኢትዮጵያ” በሚል የመሰረቱት ድርጅት የመጀመሪያ የኢትዮጵያ ጉዞውን ባለፈው የካቲት ወር አድርጎ እንደነበር ፎክስ ኒውስ በዘገባው አስታውሶ፤ በወቅቱ ለ32 ህሙማን የቀዶ ህክምና የሰጠ ሲሆን፤ በነሃሴ ወር ለሚኖረው ተመሳሳይ አገልግሎት  መነሻዎችን አስቀምጦ መመለሱን አመላክቷል።

የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ኦብሲኔት “አሁን የምናደርገው በዓመት ውስጥ በዘርፉ መሰራት ከሚኖርብን በጣም ጥቂቱን መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል” ብለዋል።

በየካቲት ወር አገልግሎቱን ለመስጠት በመጡበት ወቅት  350 ሺህ የአሜሪካን ዶላር የሚገመቱ  የተለያዩ የህክምና ቁሳቁስ  ከስድስት ባለሙያዎች ጋር ይዘው እንደመጡ ጠቅሰው፤ አሁን  የባለሙያዎች ቁጥር ወደ 16 ከፍ ማለቱን መግለጻቸውን ዘገባው አመላክቷል።


 

ዶክተር ኦብሲኔት አክለውም በነሐሴው ወር የአገልግሎት መርሃግብር ለ20 ህሙማን የልብ ከፍቶ ማከምን ጨምሮ ከ70 ለሚበልጡ ህሙማን የቀዶ ህክምና እንደሚሰጥ አስታውቀዋል።

በመርሃ ግብሩ ከአንድ ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ የሚገመቱ የህክምና ቁሳቁሶችንም ይዘው ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡ ተገልጿል።

የዶክተር ኦብሲኔት ታናሽ እህትን ጨምሮ የቅርብ የሚሏቸውን የቤተሰቦቻቸው አባላት በህክምና እጦት ምክንያት በሞት ማጣታቸው ወገኖቻቸውን በሙያቸው ለመርዳት ገፊ ምክንያት እንደሆናቸውም ዶክተሮቹ ተናግረዋል ሲል ፎክስ ኒውስ በዘገባው አመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም