የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር እና ተጠሪ ተቋማቱ ለጎፋ ዞን አደጋ ተጎጂዎች ድጋፍ አደረጉ - ኢዜአ አማርኛ
የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር እና ተጠሪ ተቋማቱ ለጎፋ ዞን አደጋ ተጎጂዎች ድጋፍ አደረጉ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 24/2016(ኢዜአ)፦የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር እና ተጠሪ ተቋማቱ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ በመሬት መንሸራተት አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ድጋፍ አደረጉ።
የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር)፤ በተቋማቱ በድምሩ የተደረገውን የ10 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ተረክበዋል።
በደረሰው አደጋ ተጎጂዎችን ለመደገፍና በዘላቂነት ለማቋቋም የተቀናጁ ተግባራት እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
ለመልሶ ማቋቋምና አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ እየተደረገ ያለው ርብርብም ተጠናክሮ መቀጠሉን ኮሚሽነር ሽፈራው ገልጸዋል።
በዛሬው ዕለትም በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር እና ተጠሪ ተቋማቱ ለተደረገው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በክረምቱ መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ በሚኖርባቸው አካበቢዎች አደጋ እንዳይከሰት ጥንቃቄ እንዲደረግ አስገንዝበው ሊደርስ ከሚችል አደጋን አስቀድሞ ለመከላከል ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል
የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ሀብታሙ ሃይለሚካኤል፤ በአደጋው ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች በተቋማቱ በዛሬው እለት ድጋፍ መደረጉን ጠቅሰዋል።
በቀጣይም መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ርብርብ ድጋፋችን ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ አረጋግጠዋል።