በምክክሩ አካል ጉዳተኞች አጀንዳቸውን ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከማሳወቅ ባሻገር በሂደቱ በባለቤትነት ስሜት መሳተፍ አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
በምክክሩ አካል ጉዳተኞች አጀንዳቸውን ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከማሳወቅ ባሻገር በሂደቱ በባለቤትነት ስሜት መሳተፍ አለባቸው
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 24/2016(ኢዜአ)፦ በምክክሩ አካል ጉዳተኞች አጀንዳቸውን ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከማሳወቅ ባሻገር በሂደቱ በባለቤትነት ስሜት መሳተፍ እንዳለባቸው የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽነር አምባዬ ኦጋቶ(ዶ/ር) ገለጹ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር በምክክሩ ሂደት የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎና ሚና ላይ ያተኮረ ሁለተኛው ዙር ሀገር አቀፍ የምክክር መድረክ በሐዋሳ ከተማ እያካሄደ ይገኛል።
መድረኩን በንግግር የከፈቱት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽነር አምባዬ ኦጋቶ(ዶ/ር) በኢትዮጵያ በተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችና በሀሳብ መሪዎች መካከል የሚስተዋሉ መሠረታዊ የሆኑ ልዩነቶችንና ሀገራዊ ችግሮችን በምክክር ለመፍታት በአዋጅ የተቋቋመው ኮሚሽን በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
ሀገሪቱ በሚያጋጥሟት ግጭቶች አካል ጉዳተኞች ግንባር ቀደም ተጎጂዎች በመሆናቸው ችግሮቹን በውይይት ለመፍታት በሚደረገው ሂደት ትርጉም ያለው ተሳትፎ ሊያደርጉ እንደሚገባ ተናግረዋል።
በመሆኑም በምክክሩ አካል ጉዳተኞች አጀንዳቸውን ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከማሳወቅ ባሻገር በሂደቱ በባለቤትነት ስሜት መሳተፍ እንደሚገባቸው ኮሚሽነሩ አሳስበዋል፡፡
የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይነህ ጉጆ በበኩላቸው በሀገሪቱ በሚፈጠሩ አለመግባባቶችና ግጭቶች ሁሉም ማህበረሰብ ተጎጂ ቢሆንም አካል ጉዳተኞች ግን የከፋ ተጎጂ መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
ችግሮችን በምክክር በመፍታት ሂደት የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎ እጅግ በጣም አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።
የምክክር መድረኩ ተሳታፊ የአካል ጉዳተኞች ተወካዮች ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ፣ ችግሮችን በዴሞክራሲያዊ ውይይት የመፍታት ባህል እንዲያዳብሩ አሳስበዋል።
የሐዋሳው የአካል ጉዳተኞች የምክክር መድረክ ዛሬና ነገ የሚቀጥል ሲሆን ከክልሎች፣ ከከተማ አስተዳደሮች፣ ከተለያዩ የአካል ጉዳተኞች ማህበራትና ከአካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን የተውጣጡ ተወካዮች እየተሳተፉበት ይገኛሉ፡፡