የኮኮስ አባላቱ የሴቶች ተጠቃሚነት ትኩረት አድርገው ይሰራሉ - አፈ ጉባዔ አሲያ ከማል - ኢዜአ አማርኛ
የኮኮስ አባላቱ የሴቶች ተጠቃሚነት ትኩረት አድርገው ይሰራሉ - አፈ ጉባዔ አሲያ ከማል

ሠመራ ፤ ሐምሌ 24/2016(ኢዜአ)፦ የኮኮስ አባላቱ የሴቶች ተጠቃሚነት ላይ ትኩረት አድርገው እንደሚሰሩ የአፋር ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አሲያ ከማል ተናገሩ።
ሴት የምክር ቤት አባላት(ኮከስ) የሴቶችን ተጠቃሚነት ሊያረጋግጡ በሚችሉና የሴቶች ጉዳዮችን በየደረጃው ማስፈፀም በሚያስችል የበጀት ምደባ ላይ ትኩረት ያደረገ ስልጠና በክልሉ ሰመራ ከተማ እየተሰጠ ነው።
የአፋር ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ወይዘሮ አሲያ ከማል በመድረኩ እንደተናገሩት ኮከሱ ለሴቶች ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ላይ በርካታ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል።
የሴቶችን ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማረጋገጥ የሚቻለው ደግሞ በተቋማት ውስጥ የሴቶች ጉዳዮችን ትኩረት ሰጥቶ በበጀት የተደገፈ ስራዎችን ማከናወን ሲቻል ነው ብለዋል።
ስለሆነም ጊዜውን የጠበቀ ትኩረት ተሰጥቶ በበጀት እንዲደገፍ የምክር ቤት አባላቱ ግንዛቤያቸውን እያሳደጉ መሄድ አለባቸው ብለዋል።
የክልሉ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ፋጡማ መሐመድ በበኩላቸው ሴቶችን በሁለንተናዊ ጉዳዮች በየደረጃው ተጠቃሚ ለማድረግ ትኩረት ተደርጓል ብለዋል።
ሴቶችን ተጠቃሚ ማድረግ ማህበረሰብን ተጠቃሚና ተገልጋይ ማድረግ መሆኑን ተረድተን የሚሰሩ ስራዎች በበጀት የተደገፉ እንዲሆኑና የተሻለ መሥራት እንዲቻል በሙሉ አቅም እንንቀሳቀሳለን ብለዋል።
ይህም የሴቶች አቅምና ችሎታ በየዘርፉ እንዲወጣ ከማስቻሉም ባሻገር በዕቅድ የታገዘ ስራ ተሰርቶ የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት ያስችላል ብለዋል።
ለሴት የኮከስ አባላቱ ስልጠናውን እየሰጡ ያሉት በሰመራ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት አኒሳ ኡመር እንደተናገሩት የሴቶች ውሳኔ ሰጭነትን ማሳደግ የሚቻለው ትኩረት ተደርጎ ሲሰራ ነው።
ሥልጠናው ሴቶች አቅማቸውን ተጠቅመውና በበጀት ተደግፈው መሥራት እንዲቻል የሚያግዝ መሆኑን ገልፀው፤ ይሄም እንደ አገርም ትኩረት የተደረገበት መሆኑን አስታውሰዋል።