ቀጥታ፡

በሲዳማ ክልል የቡና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚከናወኑ ውጤታማ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 24/2016(ኢዜአ)፦ የቡና ምርት ምርታማነትን ለማሳደግ የተከናወኑ ውጤታማ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የሲዳማ ክልል የቡና፣ ፍራፍሬና ቅመማቅመም ባለሥልጣን ገለጸ።

 በባለሥልጣኑ የልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር ምንዳዬ ምትኩ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የሲዳማ ክልል በቡናው ዘርፍ ከፍተኛ ምርትና በገበያ ተፈላጊ የሆነ የልዩ ጣዕም ቡና ጸጋ ባለቤት ነው። 

ይህንንም ተከትሎ ባለፉት ሦስት ዓመታት ኩታገጠም የቴክኖሎጂ መንደር በመመሥረት የቡና ምርትና ምርታማነትን  የማሳደግ ሥራ ተፈጥሯዊ ጣዕምን በጠበቀ መልኩ ለማምረት የሚያስችሉ ፓኬጆች ተዘጋጅተው እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። 

ከዚህ ውስጥ ያረጁ ቡናዎች ለአካባቢው ተስማሚ በሆኑ ምርታማ ችግኝ መተካት፣ ማደስ፣ የቡና ቁመት መግታት፣ የተከላ ሂደትን ሳይንሳዊ አሠራርን ጠብቆ የማከናወንና ሌሎች ተግባራት ትኩረት የተሰጠው መሆኑን ገልፀዋል።  

በክልሉ ያሉ 450 የቡና ማዘጋጃ ኢንዱስትሪዎችና ሞዴል አርሶ አደሮች ከቡናና ከሌሎች ምርቶች ከሚገኙ ተረፈ ምርቶችን ኮምፖስት በማዘጋጀት ለራሳቸውና ለአካባቢው አርሶ አደሮች ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል። 

በተጨማሪም ለአካባቢው አርሶ አደሮች ምርጥ የቡና ችግኝ አቅርቦት፣ የእንክብካቤ ሥራና የቡና ጥራት አጠባበቅ ሥልጠና ከመስጠት ባሻገር የተሻለ ገበያ አርሶ አደሮች እንዲያገኙ አስተዋጽዖ እያደረጉ ይገኛሉ ብለዋል። 

በክልሉ የሚገኙ ሞዴል አርሶ አደሮች በሄክታር ከ15 ኩንታል በላይ እያመረቱ የሚገኙ ሲሆን፤ መደበኛ አርሶ አደሮች ደግሞ 9 ነጥብ 64 ኩንታል በማምረት ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ገልፀዋል። 

በቀጣይ ዓመትም አርሶ አደሮቹ በሄክታር 10 ነጥብ 24 ኩንታል ምርት የሚገኝ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ክልሉ በቡናው ዘርፍ ያለውን ልዩ ፀጋ በአግባቡ ለመጠቀም የተከናወነው ተግባር ውጤታማ በመሆኑ የአርሶ አደሮችን የምርታማነት አቅም ሞዴል አምራቾች በደረሱበት ደረጃ ለማድረስ የተጠናከረ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልፀዋል። 

በአንዳንድ አካባቢዎች ልዩ ድጋፍ ተሰጥቷቸው ምርታማነትና የቡና ጥራት የማስጠበቅ ሥራ በተከናወነባቸው አካባቢዎች የተሻለ ደረጃ ያለው ቡና ለማዕከላዊና ለዓለም አቀፍ ገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆን መጀመራቸውን ተናግረዋል።  

ከእነዚህም መካከል የባለ ልዩ ጣዕም ቡና ውድድርም በከፍተኛ ደረጃ በማሸነፍ ከፍተኛ ገቢ ለግልና ለአገር እያስገኙ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዚህም መሠረት ኢትዮጵያ ባለፉት ሦስት ዓመታት በተወዳደረችባቸው የባለ ልዩ ጣዕም ውድድር ከፍተኛ ሽልማት ያሸነፉ ቡና አምራች አርሶ አደሮች በሁሉም ዓመት መኖራቸውን አስታውቀዋል።  

ለአብነትም በዘንድሮ ዓመት በተካሄደው ውድድር በእጅጉ ጨምሮ ለዓለም አቀፍ ውድድር ካለፉ 40 ተወዳዳሪዎች ውስጥ 34ቱ ቡና አምራች አርሶ አደሮች ከሲዳማ ክልል መሆናቸው ገልፀዋል። 

በዚህም ለዓለም አቀፍ ገበያ በርካታ የልዩ ጣዕም ቡና አቅራቢዎች ማፍራት የተቻለ መሆኑን አንስተዋል።

ለዚህም ውጤት በቡናው ዘርፍ የተደረገው የማሻሻያ ሥራዎች አርሶ አደሮቹና አቅራቢዎች በቀጥታ ተጠቃሚ ያደረገ መሆኑን አስረድተዋል። 

በተለይም በደጋማና ከፊል ደጋማ  አካባቢ ያሉ አርሶ አደሮች የተሻለ ተፈላጊነት ያለው የቡና ጣዕም በማምረት እየተጠቀሙ መሆኑን አንስተው፤ የአካባቢውን  የተፈጥሮ ጸጋ በአግባቡ ለመጠቀም በማለም ልዩ ድጋፍ ሲሰጥ እንደነበር አስታውሰዋል።

በቀጣይም በተፈጥሮ የተገኘውን ጸጋ በአግባቡ ለመጠቀም ትኩረት አድርገው እንደሚሰሩ ገልፀዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም