በሲዳማ ክልል ወንሾ ወረዳ በተከሰተ የመሬት መንሸራተት አደጋ ከቄያቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን ለማቋቋም እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሲዳማ ክልል ወንሾ ወረዳ በተከሰተ የመሬት መንሸራተት አደጋ ከቄያቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን ለማቋቋም እየተሰራ ነው

ሀዋሳ፤ ሐምሌ 24/2016(ኢዜአ)፦በሲዳማ ክልል ወንሾ ወረዳ በተከሰተ የመሬት መንሸራተት አደጋ ከቄያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ በዘላቂነት ለማቋቋም ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ።
የወንሾ ወረዳ አደጋና ስጋት መከላከል ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ክፍሌ ቲያ እንደገለጹት፣ ሐምሌ 21 ቀን 2016 ዓ.ም ከሌሊቱ 10 ሰዓት ጀምሮ በጣለው ከባድ ዝናብ በወረዳው ሦስት ቀበሌዎች ውስጥ ከፍተኛ የመሬት መንሸራተት አደጋ ተከስቷል።
በአደጋው የ10 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ በእንስሳት፣ በለማ ሰብልና እንሰት እንዲሁም በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ጠቁመዋል።
የወረዳው አስተዳደር ከክልሉ መንግስት ጋር በመሆን አደጋው ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
በአደጋው ምክንያት ከ7 ሺህ ባላይ አባውራዎች ከነቤተሰቦቻቸው ከቄያቸው ተፈናቅለው በሦስት ማዕከላት በሚገኙ ትምህርት ቤቶች መጠለላቸውን የገለጹት ኃላፊው፣ ለተፈናቀሉት ወገኖች የእለት ደራሽ እርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑን አስረድተዋል።
በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸው ስድስት ሰዎች በይርጋለም ሆስፒታል ህክምና እንዲያገኙ መደረጉንም አቶ ክፍሌ አስታውቀዋል።
ድጋፉን በተደራጀ አግባብ ለማከናወን የተጎጂዎችና የጠፋው ንብረት ልየታ መከናወኑን ጠቅሰው፣ ተጎጂዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ከአደጋው ተጎጂዎች መካከል በወረዳው የሆሞ ቀበሌ ነዋሪ አቶ መንግስቱ ማጆ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ባለፈው እሁድ በአካባቢያቸው የጣለውን ከባድ ዝናብ ተከትሎ በተከሰተ የመሬት መንሸራተት በቤተሰባቸው እና በንብረት ላይ ጉዳት ማድረሱን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት ከቄያቸው ተፈናቅለው መንግስት ባመቻቸላቸው መጠለያ ውስጥ ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንደሚገኙ ገልጸው መንግስትና ህዝብ እያደረገላቸው ላለው ድጋፍ አመስግነዋል።
በተያያዘ ዜና የሲዳማ ልማት ማህበር በወረዳው ወንሾ ወረዳ በተከሰተው የመሬት መንሸራተት አደጋ ከቄያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ዛሬ የቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።
የማህበሩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ወይንሸት መንገሻ ድጋፉን በወረዳው ተገኝተው ሲያስረክቡ እንደገለጹት አደጋው ለሰዎች ህይወት ማለፍ ምክንያት በመሆኑ የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ገልፀዋል።
ማህበሩ ከቆመለት ዓላማ አንዱ በድንገተኛ አደጋ ለጉዳት የሚዳረጉ ወገኖችን መደገፍ መሆኑን ጠቁመው፣ በድጋፉ 350 ሺህ ብር የሚገመት የምግብና የአልባሳት ድጋፍ ተደርጓል ብለዋል።
ማህበሩ ዛሬ ያደረገው ድጋፍ የመጀመሪያ መሆኑን ጠቁመው፣ በቀጣይም ማህበሩ የክልሉን ህዝብና ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር ከተጎጂ ወገኖች ጎን እንደሚቆም አረጋግጠዋል።
የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ በወንሾ ወረዳ በተከሰተው የመሬት መንሸራተት አደጋ ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች በስፍራው ተገኝተው ያጽናኑ ሲሆን በይርጋለም ሆስፒታል ሕክምና ኮሌጅ ሕክምናቸውን እየተከታተሉ ያሉ ተጎጂዎችንም መጠየቃቸው ይታወሳል።