በበጀት ዓመቱ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅ የሚያስችሉ የፓርላማ ዲፕሎማሲ ተግባራት ተከናውነዋል - ፈትሂ መሀዲ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
በበጀት ዓመቱ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅ የሚያስችሉ የፓርላማ ዲፕሎማሲ ተግባራት ተከናውነዋል - ፈትሂ መሀዲ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 24/2016 (ኢዜአ)፦በተጠናቀቀው የ2016 በጀት ዓመት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅ የሚያስችሉ ስኬታማ የፓርላማ ዲፕሎማሲ ተግባራት ማከናወን እንደተቻለ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ፈትሂ መሀዲ (ዶ/ር) ገለጹ።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ፈትሂ መሀዲ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት በበጀት ዓመቱ የኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ጥቅም የሚያስጠብቁ የዲፕሎማሲ ስራዎች ተከናውነዋል።
የፓርላማ ዲፕሎማሲ ስራዎች ከተለያዩ አገራት ዲፕሎማቶች፣ አምባሳደሮችና የምክር ቤት አባላት ጋር መካሄዱን ገልጸዋል።
በነዚህ ግንኙነቶችም የኢትዮጵያን አቋም በሚገባ ማንጸባረቅ የተቻለበትና የህዝብን ጥቅምና የሀገር ፍላጎት ለማሳወቅ በቂ ዝግጅት ተደርጎባቸው የተከናወኑ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
እንዲሁም የኢትዮጵያን የመልማት ፍላጎት በሰላም የመኖርና ከሌሎች አገራት ጋር ተቀራርቦ የመስራት ፍላጎት ማመላከት መቻሉን ተናግረዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ኢሳ ቦሩ በበኩላቸው ለቀጣናው ሰላም መፍጠር በሚችሉ ጉዳዮች የተለያዩ ውይይቶች መደረጋቸውን ጠቁመዋል።
በዚህም ብሔራዊ ጥቅምንና የኢትዮጵያን ሉአላዊነት የሚያስጠብቁ ዲፕሎማሲያዊ ስራዎች መሰራታቸውን ተናግረዋል።
የተከናወኑ የዲፕሎማሲያዊ ስራዎች ብሔራዊ ጥቅምን ማዕከል ያደረጉ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል ሞጋ አባቡልጋ ናቸው።
የፓርላማ ዲፕሎማሲ ስራ ብዥታ የፈጠሩ ጉዳዮችን በማጥራት አገራት የተሻለ ግንዛቤ እንዲይዙ የሚያስችላቸው ስራ መሰራቱን አመላክተዋል።