በደሴ ከተማ የተከሰተውን የመሬት መንሸራተት ተከትሎ ለአደጋ ተጋላጭ ለሆኑ ወገኖች ጊዜያዊና ዘላቂ መፍትሄ ለማመቻቸት እየተሰራ ነው

ደሴ፤ ሐምሌ23 /2016(ኢዜአ)፡- በደሴ ከተማ አስተዳደር የተከሰተውን የመሬት መንሸራተት ተከትሎ ለአደጋ ተጋላጭ ለሆኑ ወገኖች ጊዜያዊና ዘላቂ መፍትሄ ለማመቻቸት እየተሰራ መሆኑን የከተማው አስተዳደር ገለጸ።

የከተማ አስተዳደሩ ከተማና መሰረት ልማት መምሪያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ቃሲም አበራ እንዳመለከቱት፤   በአስተዳደሩ ቀደም ሲል የጎርፍ አደጋ ለመከላከል ከስድስት ሚሊዮን ብር በሚበልጥ በጀት የጎርፍ መፋሰሻና መቀልበሻ ቦይ እንዲሁም የድጋፍ ግንብ እየተሰራ  ነው።

ሆኖም  ትናንት ማታ የጣለው ከባድ ዝናብ ተከትሎ በከተማው አራዳ ክፍለ ከተማ ጀሜ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የመሬት መንሸራተት መከሰቱን ተናግረዋል።



በዚህም በመኖሪያ ቤቶች፣ በእምነት ቦታዎች፣ ከደሴ ከተማ ወደ ደቡብ ወሎ ዞን ምዕራብ ወረዳዎች የሚወስደው አስፋልት መንገድ ላይ ጉዳት መድረሱን ገልጸዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ትኩረት በመስጠት  ለስጋት የተጋለጡ ወገኖችን ለመታደግ ኮሚቴ አቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱን አስታውቀዋል።

ለአደጋው ስጋት የተጋለጡ ወገኖችን ጊዜያዊና  ዘላቂ መፍትሄ ለማመቻቸትም አስተዳደሩ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ህብረተሰቡ በክረምቱ ከሚጥለው ዝናብ ጋር ተያይዞ በሚከሰት ጎርፍ ጉዳት እንዳይደርስ የተዘጉ  የጎርፍ መውረጃ ቦዮችን እንዲያፀዳ መልዕክት አስተላልፈዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም