መከላከያ ሠራዊትን መደገፍ የኢትዮጵያን ክብር መጠበቅ ነው - የዳያስፖራ አባላት - ኢዜአ አማርኛ
መከላከያ ሠራዊትን መደገፍ የኢትዮጵያን ክብር መጠበቅ ነው - የዳያስፖራ አባላት
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 23/2016(ኢዜአ)፦ መከላከያ ሠራዊትን መደገፍ የኢትዮጵያን ክብር መጠበቅ መሆኑን በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ገለጹ፡፡
በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ ለኢትዮጵያ ቀናዒ እሳቤ ያላቸው ኢትዮጵያውያንና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን የመከላከያ ሠራዊቱን በመደገፍ ለሀገር አለኝታነታቸውን እያሳዩ ነው፡፡
እነዚህ ዜጎች ለሀገር ማድረግ የሚገባቸውን አስተዋፅዖ ለማበርከት "ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያውያን ዳያስፖራ ለብልጽግናና ብዝኃነት" የተሰኘ ድርጅት መስርተው እንቅስቃሴ ጀምረዋል፡፡
ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያውያን ዳያስፖራ ለብልጽግናና ብዝኃነት ፕሬዝዳንት ጋሻው ቢርቦ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ማኅበሩ የተመሠረተው የኢትዮጵያን ልዕልና ለማብሰር ከተናጠል ይልቅ በጋራ መቆም የተሻለ መሆኑ ስለታመነበት ነው፡፡
ለዚህም የለውጡን መንግሥት የሚደግፉ፣ ሀገራቸውን የሚወዱ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን በጋራ ተሰባስበው የመሠረቱት መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በሰሜን አሜሪካ የጋምቤላ ክልል ዳያስፖራ ማኅበረሰብ ፕሬዝዳንት ዲዱሞ አሌሞ፤ የመጣነው መከላከያ ሠራዊት የሀገራችንን ህልውና ለማስጠበቅ ለሚከፍለው መስዋዕትነት ምስጋና ለማቅረብ ነው ብለዋል።
ለዚህም በመጀመሪያው ጉዟችን ኮምፒውተርና መሰል ቁሳቁሶችን በመያዝ ከሠራዊቱ ጎን መሆናችንን በተግባር አሳይተናል ሲሉ ተናግረዋል።
የድርጅቱ ኮሙኒኬሽን ኃላፊ ሰላማዊት ዋቆ፤ ሀገራችንን በምንችለው አቅም መደገፍ አለብን ስንል ቅድሚያ የሰጠነው ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ነው ብለዋል፡፡
የመከላከያ ሠራዊት ውድ ህይወቱን እየሰጠ ለኢትዮጵያ ክብርና ሉዓላዊነት ለሕዝቦች ሰላም ዋጋ እየከፈለ በመሆኑ ከምንም በላይ ለሠራዊቱ ቅድሚያ ሰጥተናል ሲሉ ተናግረዋል።
መከላከያ ሠራዊትን መደገፍ የኢትዮጵያን ክብር የመጠበቅና ሕዝቦቿን ከብተና መታደግ በመሆኑ በርቀት የሚተቹ አካላት ቀርበው እውነቱን ማረጋገጥ እንዳለባቸው ገልፀዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን ያለችን አንድ ሀገር ናት የሚሉት የዳያስፖራ አባላቱ፤ የሀገር ህልውናን የሚያስጠብቅ ሠራዊትን መደገፍ አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ-ኢትዮጵያውያንን በማስተባበር ጠንካራ አደረጃጀት መፍጠርና ከኢትዮጵያ ሁለንተናዊ እድገት ጎን መቆም የቀጣይ የቤት ሥራችን ነው ሲሉም አረጋግጠዋል።
የመከላከያ ሠራዊት መኮንን ኮሎኔል ሲራጅ ሲንብሩ፤ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ- ኢትዮጵያውያን የሚያደርጉት ድጋፍ ለሠራዊቱ የሞራል ስንቅ ይሆናል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሀገሩን ሉዓላዊነትና የዜጎችን ደኅንነት ለማስጠበቅ የሚዋደቅ ጀግና ሠራዊት መሆኑን ገልጸው፤ ለዚህ ዋጋው ድጋፍና እውቅና መስጠቱ ትልቅ የሞራል ስንቅ መሆኑን ገልፀዋል።
ለኢትዮጵያ ሰላም ልማትና ብልፅግና መረጋገጥ በሀገር ቤትም ይሁን ውጭ የሚኖሩ ዜጎች እገዛና ትብብር ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።