ቀጥታ፡

ኢመደአ በወንጀል መከላከልና በምርመራ ሥራ ከፍተኛ ድጋፍ በማድረጉ ከውስጥም ከውጭም የተሰነዘሩ የወንጀል ድርጊቶችን መከላከል ተችሏል-ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 23/ 2016(ኢዜአ)፡- የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) በወንጀል መከላከልና በምርመራ ሥራ ከፍተኛ የቴክኒክ እና የማቴሪያል ድጋፍ በማድረጉ በሀገራችን ላይ ከውስጥም ከውጭም የተሰነዘሩ የወንጀል ድርጊቶችን መከላከል መቻሉን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለጹ።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል እና የማኔጅመንት አባላት የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደርን ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱ ወቅትም  የፀጥታ ተቋማትን ለማገዝና ለሳይበር ጥቃት ተጋላጭ የሆኑ የግልና የመንግስት ተቋማትን ለመጠበቅ እየተሠሩ ያሉ ተግባራትንና የሳይበር ጥቃቶች ለመመከት እየዘመኑ ያሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ተመልክተዋል። 


 

ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ከጉብኝቱ በኋላ በነበረው ውይይት ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ኢመደአ በአጭር ዓመታት ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ እራሱን እያዘመነ የመጣና ለፀጥታ ተቋማትም ዋነኛ አጋር ሆኖ የዘለቀ ተቋም መሆኑን ገልጸዋል።
 
በዚህም ተቋሙ ሀገራችን ለደረሰችበት ሁለንተናዊ ዕድገት አስተዋፅኦው ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል። 

ኮሚሽነር ጀነራሉ አያይዘውም ኢመደአ በወንጀል መከላከልና በምርመራ ሥራ ከፍተኛ የቴክኒክ እና የማቴሪያል ድጋፍ ለኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በማድረጉ በሀገራችን ላይ ከውስጥም ከውጭም የተሰነዘሩ የወንጀል ድርጊቶችን መከላከል ተችሏል ብለዋል። 

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ትዕግስት ሀሚድ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እና ኢመደአ ጠንካራና እያደገ የመጣ የሥራ ግንኙነት እንዳላቸው ገልጸዋል። 

በቀጣይም ትብብሩን የበለጠ በማጠናከር በጋራ እንደሚሰሩ መገለጹን ከፌደራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም