የኅብረተሰብን ጤና ለመጠበቅ የሚያስችሉ ምርምሮችና የመረጃ ማጠናቀር ሥራዎች እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኅብረተሰብን ጤና ለመጠበቅ የሚያስችሉ ምርምሮችና የመረጃ ማጠናቀር ሥራዎች እየተከናወኑ ነው
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 23/2016 (ኢዜአ)፦ የኅብረተሰብን ጤና ለመጠበቅ የሚያስችሉ ምርምሮችና የመረጃ ማጠናቀር ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
ኢንስቲትዩቱ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የክልል ጤና ቢሮ፣ የአጋር ድርጅት ኃላፊዎችና ተወካዮች በተገኙበት የጤና መረጃ፣ የመሰብሰብ፣ የማጠናከር የመተንተን እና ለውሳኔ መጠቀም ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ አካሂዷል።
በዚሁ መድረክ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር መሳይ ኃይሉ(ዶ/ር)፤ የዜጎችን ጤና ለመጠበቅ የሚያስችሉ ምርምሮችና የመረጃ ማጠናቀር ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በሀገር አቀፍ ደረጃ ያሉ የላቦራቶሪ አቅሞችንና አጠቃላይ የጤና መረጃዎችን በአንድ ቋት በማሰባሰብ ጥቅም ላይ የማዋል ሥራ ተጀምሯል ብለዋል።
በዚሁ መሠረት 36 የበሽታ አይነቶችና የጤና ስጋቶችን በመለየት መረጃ በመሰብሰብ፣ በማጠናቀርና በመተንተን ለውሳኔ እየተጠቀምንበት ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በኢንስቲትዩቱ የመረጃ ማዕከል ከ500 በላይ የጤና እና ጤና ነክ መረጃዎች ተደራጅተው አገልግሎት እየሰጡ መሆኑንም ገልፀዋል።
በዚህም የበሸታዎችን ሥርጭት በመከታተል የቅድመ ትንበያ፣ የዝግጁነት፣ የመከላከል፣ የመቆጣጠርና የምላሽ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።
ኢንስቲትዩቱ በዋነኝነት መረጃዎችን መሠረት በማድረግ ነባርና አዳዲስ የስጋት ቀጣናዎችን በመለየት የማኅበረሰቡን ጤና የመጠበቅ ሥራ እያከናወነ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የጤና ፕሮግራሞችን ለመቅረጽ፣ ለማሻሻል፣ ለዕቅድ፣ ለጥናትና ምርምር እንዲሁም ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ ጥናታዊ መረጃዎችን ተደራሽ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በኢንስቲትዩቱ የብሔራዊ የጤና መረጃ አስተዳደር ቅመራና ትንተና ማዕከል ዳይሬክተር አስናቀ ወርቁ (ዶ/ር)፤ የኅብረተሰብ ጤና አደጋ መረጃ፣ የላቦራቶሪ፣ የሚቲዎሮሎጂ፣ የትራፊክ አደጋና ሌሎችም በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጠኑ ግኝቶች መኖራቸውን ገልፀዋል፡፡
በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ3 ሺህ 500 በላይ የጤናና ጤና ነክ መረጃ በተለያዩ ተቋማት መኖራቸውን ጠቅሰው፤ በቀጣይ በኢንስቲትዩቱ ማዕከል ለማሰባሰብ መታቀዱን ተናግረዋል።
የማዕከሉ አሠራር ውጤታማ በመሆኑ በአፍሪካ የበሽታዎች መከላከያና መቆጣጠሪያ ማዕከል አማካኝነት በአሥር ሀገራት እንዲተገበር እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።