ቀጥታ፡

ጉምሩክ ኮሚሽን እና ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በጎፋ ዞን በመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ አደረጉ

 ጎፋ ሳውላ ፤ ሐምሌ 23/2016(ኢዜአ)፦ ጉምሩክ ኮሚሽን እና ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ በደረሰ የመሬት መንሸራተት አደጋ ቤተሰቦቻቸውን ላጡና ለተፈናቀሉ ወገኖች የገንዘብና የአይነት ድጋፍ አድረጉ።

የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ እንዲሁም የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አያኖ በራሶ (ዶ/ር) ይዘው የመጡትን የገንዘብና አይነት ድጋፍ ዛሬ ለዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ዳግማዊ አየለ አስረክበዋል።

ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ ድጋፋን ባስረከቡበት ወቅት እንደገለጹት በወገኖች ላይ የደረሰው ድንገተኛ አደጋ የሁሉንም ልብ የሰበረ ነው።

በአይነት ያደረጉት ድጋፍ 8 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር እንደሚገመት ገልጸው፣ በድጋፉ ለዕለት የሚሆኑ የተለያዩ ምግቦችና ቁሳቁስ መካተታቸውን ጠቅሰዋል።

በጥሬ ገንዘብም 5 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር መለገሱን ገልጸው በቀጣይም የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል።


 

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አያኖ በራሶ (ዶ/ር) በበኩላቸው ድንገተኛ የመሬት መንሸራተት አደጋው  የበርካታ ወገኖችን ሕይወት የቀጠፈና አሳዛኝ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ዩኒቨርሲቲው አደጋው እንደተሰማ 21 የሕክምና ባለሙያዎችንና 3 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው መድኃኒትና የሕክምና ቁሶችን ፈጥኖ በመላክ ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰዋል።

ዛሬም በጥሬ ገንዘብ አንድ ሚሊዮን ብር እንዲሁም የምግብና የአልባሳት ድጋፍ መደረጉንና በቀጣይም የጀመሩትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ዳግማዊ አየለ አደጋው የከፋ እና ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ያሳዘነ  መሆኑን አስታውሰው።

ጉሙሩክ ኮሚሽንና ዩኒቨርሲቲው ተጎጂዎችን ከማጽናናት ባለፈ ላደረጉት ወገናዊ ድጋፍ አስተዳዳሪው ምስጋና አቅርበዋል።

ኢንጂነር ዳግማዊ እንዳሉት በአደጋው ቤተሰቦቻቸውን ላጡና ለተጎዱ ወገኖች የሚደረገው ድጋፍ አሁንም ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን፣ በቀጣይም ተጎጂዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም በትኩረት ይሰራል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም