የኢትዮ-ቻይና የሚዲያ ዘርፍ ትብብር በብሪክስ ማዕቀፍ ሊጠናከር ይገባል- ቻይናዊያን ጋዜጠኞችች - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮ-ቻይና የሚዲያ ዘርፍ ትብብር በብሪክስ ማዕቀፍ ሊጠናከር ይገባል- ቻይናዊያን ጋዜጠኞችች
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 23/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮ-ቻይና ሁሉን አቀፍ ወዳጅነት በሚዲያው ዘርፍም በብሪክስ ማዕቀፍ ሊጠናከር እንደሚገባው ቻይናዊያን ጋዜጠኞች ተናገሩ።
ከቻይናው 'ፒፕልስ ደይሊ' ጋዜጣ የተወጣጣ የጋዜጠኞች ልዑክ በኢትዮጵያ የሚገኙ በቻይና በቀል ተቋራጮች የሚከናወኑ ፕሮጀክቶችን በመጎብኘት ላይ ይገኛሉ።
ከጉብኝቱ ተሳታፊዎች መካከል ኢዜአ ያነጋገራቸው ጋዜጠኞች፤ የኢትዮ-ቻይና ሁሉን አቀፍ ወዳጅነት እና ትብብር በፍጥነት እያደገ እና የህዝብ ለህዝብ ትስስርን እያጎለበተ መሆኑን ገልጸዋል።
የፒፕልስ ደይሊ ጋዜጣ ከፍተኛ ኤዲተር ሁአን ፒዥዎ እንደሚለው፤ በሁለቱ አገራት መካከል ኢኮኖሚያዊ ትስስር በሁሉም ዘርፎች እንዲጎለብት መገናኛ ብዙሃን ትልቅ ሚና ይጫወታሉ።
በአዲስ አበባ ቆይታው ሀገሬ ያለሁ ያህል ተሰምቶኛል የሚለው ጋዜጠኛው፤ የሀገራቱን ሁሉን አቀፍ ግንኙነት ለማጎልበት ሁለቱ ሀገራት በሚዲያው መስክ ትብብር ማጠናከር አለባቸው ብሏል።
ሌላኛው ጋዜጠኛ ሬን ያን በበኩሉ የኢትዮ-ቻይና ዲፕሎማሲያዊ መልካም ግንኙነት ለሚዲያዎች ትብብር መመስረት ትልቅ ዕድል እንደሆነ ተናግሯል።
በተለይም ሁለቱ ሀገራት የብሪክስ አባል መሆናችው ለትብብርና አጋርነት መጎልበት ተጨማሪ አቅም እንደሆነ ጠቅሶ፣ የሁለቱ ሀገራት የሚዲያ ትብብር በብሪክስ ማዕቀፍ ሊጠናከር እንደሚገባው ገልጿል።
ሌላኛዋ ጋዜጠኛ ሲይ ቺ፤ የኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀል ለሁለቱ ሀገራት የሁለትዮሽ ትብብር መጎልበት የማይተካ ሚና አለው ብላለች።
የኢትዮ-ቻይና በሁኔታዎች የማይለወጥ ወዳጅነት በሚዲያው ዘርፍም በብሪክስ ማዕቀፍ ሊጠናከር እንደሚገባ አንስታለች።
'ፒፕልስ ደይሊ' ጋዜጣ ልዑክ የኢትዮጵያ ጉብኝት ለቻይና ሚዲያዎች ፈር ቀዳጅ አጋጣሚ መሆኑን ጋዜጠኞቹ ገልጸው፣ ቀጣይነት ያለው ትብብር ለመመስረት በር ከፋች እንደሚሆን ተስፋ ሰንቀዋል።
በተለይም በቻይና ትልቁ ጋዜጣ 'ፒፕልስ ዴይሊ' ከኢትዮጵያ ሚዲያዎች ጋር ትብብር በመፍጠር የተሻለ ልምድና ተሞክሮ ለመቅሰም ይሰራል ብለዋል።